የሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ ተገለጸ።

56
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል። የቢሮው ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው የትንሣዔ እና የዒድ አልፈጥር በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው የክልሉ ወጣቶች እና መላው ማኅበረሰብ ለሰላም የነበረው ተሳትፎ የሚደነቅ ነበር ብለዋል።
አቶ ደሳለኝ የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ የማቋቋም እና የማደራጀት ሥራ ለማደናቀፍ ሲወራ የቆየው አሉባልታ ለሀገር ውለታ የከፈሉ የአማራ ልዩ ኀይል አባላትን ክብር የሚመጥን አልነበረም ሲሉ ገልጸዋል።
ልዩ ኀይሉ ትጥቁን ፈትቶ እና ጥቅሙ ሳይከበርለት ሊበተን እንደኾነ በማስመሰል አባላቱ ወደ ታለመው ቀጣይ ተልዕኮ እንዳይሰማራ የሴራ ቅስቀሳ ተደርጓል ነው ያሉት። በዚህም የተነሳ ያልተገባ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ቢሮ ኀላፊው አመላክተዋል።
አቶ ደሳለኝ የአማራ ልዩ ኀይል በተሠራበት አሉባልታ ልክ ያልተገኘ እና ይልቁንም ሴረኞችን ወደ ኃላ በመተው ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ቅድሚያ የሰጠ በመኾኑ ታሪካዊ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
አሁን ላይ አብዛኛው የልዩ ኀይል አባላት መብታቸው እና ጥቅማ ጥቅማቸው ተከብሮላቸው እና አጫጭር ስልጠናዎችን ወስደው ወደ ተመደቡባቸው ተቋማት በመግባት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
አሁን ያለው የክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ በአንጻራዊነት ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ የሕዝቡን የሰላም እርካታ ለማምጣት በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል። ኅብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ መንግሥት ሰላምና ጸጥታን የማስጠበቅ መደበኛ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ተፈላጊ የኾነውን ሰላም ለማምጣት መጣር እና ችግሮች ሲፈጠሩም በወያየት መፍታት አለበት ብለዋል።
የሕዝብን እና ተየቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚቀሰቅሱ አካላት አሁንም ድረስ እንዳሉ ጠቅሰዋል።የእነዚህ አካላት ዋና ዓላማ ሕዝቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ ተቋማት እንዲዘጉ እና ገበያ እንዳይኖር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅልን ለመፍጠር ያለመ ስለመኾኑም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል። በህቡዕ እየተንቀሳቀሱ ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚያደርጉ አካላት ተገቢውን እርማት እንዲያገኙ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ተቋማት በቅንጅት እየሠሩ እንደኾነም ተገልጿል። ቀጠሮ እየያዙ በየጊዜው መንገድ በመዝጋት እና የተቋማትን ሥራ በማስተጓጎል ሕዝብን ረፍት ለመንሳት በሚጥሩ አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።
ሕዝቡ እነዚህን አካላት በማጋለጥ እና ለጸጥታ ተቋማት በመጠቆም በተረጋጋ መልኩ እና በሙሉ አቅሙ ወደ ልማቱ እንዲዞርም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስፖርት ዜና ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ)
Next articleበወረዳው በመስኖ ስንዴ ከተሸፈነው ሰብል ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዳንግላ ወረዳ አስታወቀ።