
ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሀገሪቱ አጠቃላይ የእርሻ መሬት ውስጥ 39 በመቶ ገደማ ድርሻ ያለው የአማራ ክልል ከሀገራዊ ምርት 40 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ፣ ዓመቱን በሙሉ ማምረት የሚችል እና ከልማዳዊ እርሻ ፈቀቅ ብሎ መካናይዜሽንን በሰፊው የሚጠቀም ግብርናን ለመተግበር በግብርና ቤተሰብ ዘንድ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን የሚደግፍ ፣ ምርት እና ምርታማነትን ለማምጣት ያለመ የሰብል ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና በወረታ ግብርና ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተጀምሯል፡፡
የአሰልጣኖች ሥልጠናው ለምሥራቅ አማራ የዞን እና ወረዳ ግብርና ባለሙያዎች በኮምቦልቻ ከተማ ቀድሞ ተሰጥቷል፡፡ በወረታ የተጀመረው የአሰልጣኞች ሥልጣና በቀሪ የክልሉ አካባቢዎች ለሚገኙ የግብርና ቤተሰቦች የተዘጋጀ ነውም ተብሏል፡፡
የአሰልጣኞች ሥልጠናው ዋና ዓላማ በፓኬጅ ምክረ ሃሳብ አተገባበር ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ፣ የአመለካከት አንድነትን ለማምጣት እና ለምርት ዘመኑ ምቹ ኹኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ መኾን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ ካለፈው ዓመት የመኸር ምርት ዘመን በክፍተት እና ጥንካሬ በርካታ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው፤ ክፍተቶችን አርሞ ጥንካሬዎችን አስቀጥሎ የተቀመጠውን እቅድ መፈጸም የሁሉንም የግብርና ቤተሰብ ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
ክልሉ ዓመታትን ወስዶ እና ግዙፍ መዋለ ንዋይ አፍስሶ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን በርካታ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ እያገዘ ነው ያሉት አቶ ቃለኪዳን፤ የምርምር ምክረ ሃሳቦችን ተከታትሎ ማስፈጸም ላይ የሚስተዋለውን ድክመት ማረም የባለሙያውን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ መካናይዜሽንን በስፋት መጠቀም፣ ግብዓትን ማሟላት እና የአፈር ለምነትን ማከም ለምርት እና ምርታማነት እድገት ወሳኝ ናቸው፡፡ በተያዘው የመኸር ምርት ዘመን መጠነ ሰፊ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል፡፡ ዝግጅቱ በቀሪ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ባለፈው የመኸር ምርት ዘመን በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ እና አኩሪ አተርን በስፋት በመዝራት 99 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው የእነዚህ አምስት ሰብሎች አጠቃላይ የምርት ድርሻም 71 በመቶ አካባቢ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በተያዘው የመኸር ምርት ዘመንም 5 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን 154 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ መርሐ ግብር መሰረት እየተፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!