
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖች እና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በጥምረት እየሠሩ ነው።
ኑሯቸውን በመንግሥት ሥራ የሚመሩት አቶ ወንድወሰን ኀይሌ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ አዲስ ገነት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ከሚገኘው የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር የኢንዱስትሪ እና የግብርና ውጤቶችን የዱቤ አገልግሎት በማቅረባቸው በዋጋ ንረት ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር ቀንሶላቸዋል፡፡
የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በዝቅተኛ የኑሮ እርከን ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ይቀርፉ ዘንድ መንግሥት ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የሕዳሴ ዩኒየን ሥራ አሥኪያጅ ወይዘሮ ዘውድነሽ ተፈሪ፤ ዩኒየኑ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እየሠራ ነው ብለዋል። ዩኒየኑ ለአርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን ከማቅረቡ በተጨማሪ ለከተማ ነዋሪዎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እያቀረበ መኾኑን ነው ያስረዱት።
ዩኒየኑ ከዞኑ እና ከከተማ አሥተዳደሩ ባገኘው 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም ተናግረዋል።
እስካሁን 600 ኩንታል ጤፍ፣ 1 ሺህ 130 ኩንታል ዱቄት፣ 50 ካርቶን ፓስታ፣ 51 ኩንታል ማካሮኒ አቅርበዋል። ዩኒየኑ ለዱቤ አገልግሎት እየሠጠ ቢኾንም ገንዘቡ በበጀት መዝጊያ የሚመለስ በመኾኑ አገልግሎቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
በደብረብርሃን ከተማ የቀበሌ 06 አንድነት ሸማቾች ኅብርት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሀብተየስ ሽፈራው በበኩላቸው፤ የማኀበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሣደግ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
በዚህ ዓመት 233 ኩንታል ጤፍ፣ 100 ኩንታል ፊኖ ዱቄት ከማሠራጨታቸው ባሻገር በሰፊው የካፍቴሪያ አገልግሎት እየሠጡ መኾኑንም ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ አገልግሎቱን ለማከናወን ማኅበሩ የቦታ ችግር እንደገጠመው ጠቁመዋል።
የዞኑ የኅብረት ሥራ ማኅበር ማደራጃ እና ማስፋፊያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ባዩ ከበደ፤ በዞኑ የሚገኙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
የሸማች ኅብረት ሥራ ማሕበራት የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ቀጥታ ከአምራቾች እና ከፋብሪካዎች ጋር በጋራ በመሥራት ባደረጉት እንቅስቃሴ ችግሮችን መፍታት መቻላቸውን አስረድተዋል።
አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ቀጥታ ለተጠቃሚው እያቀረቡ ነው ብለዋል።
በዞኑ 276 ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 37 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና 4 ዩኒየኖች በሥራው ተሠማርተዋል።
ለዝቅተኛ ነዋሪዎች እና ለመንግሥት ሠራተኞች የግብርና ምርቶች በ3 ወር በዱቤ እና በቀጥታ ሽያጭ እየቀረበ መኾኑን አንስተዋል።
በዞኑ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ባይኖሩም ወደራ ዩኒየን ከሌሎች ዩኒየኖች ጋር ባደረገው ሥምምነት ስንዴውን አስፈጭቶ በዱቤ እያቀረበ ነው ብለዋል።
217 ሺህ 938 ሊትር ዘይት ከፋብሪካዎች በማምጣት ለሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ማሰራጨት መቻሉን አቶ ባዩ ተናግረዋል።
በርበሬ፣ ስኳር፣ ፓስታ ፣ማካሮኒ እንዲኹም ጤፍ እየተሰራጨ ነው።
ማኅበረሰቡ ኑሮውን ያለጭንቀት እንዲመራ ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ምርታቸውን እያከፋፈሉ ነው ብለዋል። ዘይት ለአርሶ አደሮች በሰፊው ቀርቧል ብለዋል። በየወረዳዎቹ አፈጻጸሙ የተለያየ ነው አቶ ባዩ እንሳሮ ወረዳ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መድቦ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ጠቁመዋል። ሌሎችም የእንሳሮን ወረዳ ልምድ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ባዩ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተዘዋዋሪ ብድር ያገኙትን 64 ሚሊየን ብር ጨምረው 214 ሚሊየን ብር ሲያንቀሳቅሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ የክረምት ወቅት የሚከሠተውን የምርት እጥረት ችግር ለመቅረፍ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!