ልጅነት እና የዒድ አልፈጥር በዓል!

55

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አሊ ሙሐመድ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ አራት ነዋሪ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ባሕርዳር ከተማ ነው፡፡ የረመዷን ጾምን ጾመው ዒድ አልፈጥርን ማክበር የጀመሩት ገና በዘጠኝ ዓመታቸው ከአባታቸው ጋር መስጅድ ሄደው ለመሥገድ በነበራቸው ፍላጎት ነው፡፡ በእሳቸው ዘመን መስጅድ ሄዶ መስገድ እንደትልቅ ነገር ይቆጠር ነበር፡፡
ጾም በሰላም ለማፍጠር የአምላክ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከአባታቸው ጋር አምላካቸውን ለማመስገን ወደ መስጅድ መሄድ የዘወትር ተግባራቸው ነበር፡፡ በዒድ አልፈጥር በዓል ዕለት ኹሌም አዲስ ልብስ መልበስ የተለመደ ባሕል ነው፡፡ አቶ አሊ ወላጆቻቸው አስበው አዲስ ልብስ ያለብሷቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር እየዞሩ ዘመዶቻቸውን እንኳን አደረሳችሁ ብለው ይዘይሩ እንደነበር አቶ አሊ ነግረውናል፡፡ የዒድ አልፈጥር በዓል ዕለት ካፈጠሩ በኋላ ወደ መስጅድ ሄደው ይሰግዱ እንደነበርም የሁልጊዜ ትዝታቸው ነው፡፡
አቶ አሊ በረመዳን ወቅት መስጅድ ማደር ቡና ማፍላት እንደብርቅ የሚታይ በመኾኑ እሳቸውም ከአባታቸው ጋር ይሄዱ እንደነበር ነግረውናል፡፡ ልጆቻቸውም በእሳቸው ልክ እንዲኾኑ ክትትል እንደሚያደርጉ አንስተዋል፡፡
ጾም የሚጾሙት በሰላም በፍቅር በሙሃባ ነበር፡፡ አቶ አሊ ልጆቻቸው እንደእሳቸው ወላጆቻቸውን አክባሪና ፈጣሪያቸውን አምላኪ እንዲኾኑ አድርገው አሳድገዋል፡፡ ከሙስሊም ባሻገር የክርስትያን ጎረቤቶቻቸው ጋር በዓሉን አብረው ያከብሩ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡ አቶ አሊ ለመጨረሻ ልጃቸው በየዓመቱ የዒድ አልፈጥር በዓል አዲስ ልብስ ሥጦታ እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ የልጅነት ትውስታቸውን ያካፈሉን ወይዘሮ ሰይዳ ገበያው ልጅነታቸውን እንደሚናፍቁት ነግረውናል፡፡ ልጅ ኾነው እድሜያቸው ሳይደርስ መጾም ጀምረዋል፡፡ በልጅነታቸው ሁለቱ ቀን እንደአንድ ቀን ይቆጠራል ስለሚባሉ እስከ ስድስት ሰዓት ብቻ ይጾሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ቤተሰቦቻቸው ጋር በግልጽ በማውራታቸው በወር አበባ ወቅት መጾም በእነሱ ቤት አይቻልም፡፡ በአረፋ እና በዒድ አልፈጥር በዓል አዲስ ልብስ መልበስ የበዓሉ አንድ ትዝታ ነው ብለዋል፡፡ ሕፃን ኾኖ መጾም መስገድ እና ዱዓ ማድረግ የተለየ ስሜት አለው፡፡ የሶላት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ነው ያሉት፡፡
ልጅ ኾነው ወላጆቻቸው ለሌለው ሲሰጡ እያዩ ያደጉት ወይዘሮ ሰይዳ ዛሬም በመስጠት መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ በልጅነታቸው ከአባታቸው ቤት በጣም ብዙ ሰው ይመጣ እና ይመገብ ሥለነበር መሥጠትን ከወላጆቻቸው ተምረዋል፡፡
ዛሬም እሳቸው ልጆቻቸው እንዲሠጡ ለማድረግ ሲሠጡ ያሳዩአቸዋል፡፡ መደባበቅ ለመጥፎ ነገር ያጋልጣልም ይላሉ፡፡ እናቶች የልጆቻቸውን ሁኔታ መረዳት አለባቸው፡፡ እነ ወይዘሮ ሰይዳ ቤት ሁሉም ግልጽ በመኾኑ የወር አበባ ኾነው ጾም ጾመው አያውቁም ፡፡ ልጆቻቸውን በዚህ ልክ ነው ያሳደጉአቸው፡፡
ወይዘሮ ሰይዳ አባታቸው አርሶ አደር ቢኾንም በዒድ በዓል ጊዜ አዲስ ልብስ ይለብሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አዲስ ልብስ መልበሥ የግድ ነው ብለዋል፡፡“ልጆቼን ሱቅ ወስጄ ልብስ አስመርጬ ገዝቼ አላውቅም፡፡ ገዝቼ አምጥቼ የበዓል ዕለት እሰጣቸዋለሁ” ብለዋል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ መሬም ማሩ ጾሙን በልጅነታቸው የጀመሩት ሾርባ ለመቀበል እንደኾነ ነግረውናል፡፡ የዒድ በዓል ልጅነት ትዝታቸው ሁሌም ከዕምሮአቸው እንደማይጠፋ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ያለው ለሌለው በማካፈል የሚደረገው ተግባር ሁሌም ለህይዎት መመሪያቸው ኾኖ እያገለገላቸው ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠትን እያስተማሩ ማሳደግ እንዳለባቸውም ወይዘሮ መሬም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?
Next articleበየጊዜው የሚከሰተውን የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ እና ማስፋፊያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።