ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?

78

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች በሰውነታቸው ብቻ የሚከበሩባት፣ ነገድ የፍቅር መነሻ እንጂ የጥል መነሻ የማይሆንባት፣ አንድነት የጸናባት፣ ፍቅርና ተድላ የበዛባት፣ በአሻገር ያያት ሁሉ የሚቀናባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?
ፍትሕ ከጠፋባት ምድር የሸሹ ፍትሕ ያገኙባት፣ የተሳደዱት ያረፉባት፣ ከእውነተኛ ንጉሥ በእውነተኛ ቤተመንግሥት የተገናኙባት፣ የተቸገሩት ተድላን ያገኙባት፣ የተራቡት የሚጎርሱባት፣ የተጠሙት የሚጠጡባት፣ ያዘኑት የሚጽናኑባት፣ ታላቅና ታናሽ የሚከባበሩባት፣ መከባበር ከፍ ያለባት፣ ወንድም ከወንድሙ ጋር የሚዋደድባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?
ፍትሕ የሰፈነባት፣ እኩልነት የታተመባት፣ የእውነት፣ በእውነት፣ ስለ እውነት የሚኖርባት፣ ነገሥታቱ የሚወዷት፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ የሚያፈቅሯት፣ በፍትሕ ሚዛን የሚጠብቋት፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚያዩባት፣ እኔ ብቻ ልብላ ሌላው ቢራብም ግድ የለኝ የማይባልባት፣ የንጹሐን እንባ በግፍ ያለ አባሽ የማይፈስስባት፣ ሕጻናት ከቀያቸው የማይሳደዱባት፣ አቅመ ደካሞች መጠለያ አጥተው ሜዳ ላይ የማይበተኑባት፣ ከዚህ መልስ የእኔ ወሰን ነው አትለፍ የማይባልባት፣ በአራቱም ንፍቅ ሰዎች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት፣ ኢትዮጵያዊነት በሚባል ውብና የማያረጅ እልፍኝ ውስጥ ደስታን የሚያዩባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?
ነብዩ መሐመድ በአሻገር ሆነው የወደዷት፣ ፍትሕ ያለባት ምድር ያሏት፣ አብዝተው የሚወዷቸው ሰዎች ይጠለሉባት ዘንድ አደራ የሰጧት፣ አደራ በሰጧትም ጊዜ አደራዋን በመወጣቷ ደስ የተሰኙባት፣ እውነተኛ ንጉሥ እንደነገሠባት የተረዱባት፣ እርሷን አትንኳት ብለው ትዕዛዝ ያስተላለፉባት፣ የእርሳቸው ሱሃባዎች ፍትሕና እውነትን፣ ፍቅርና አንድነትን፣ ሰላምና እንግዳ ተቀባይነትን ያገኙባት፣ የብስ አቋርጠው፣ ሐይቅ ሰንጥቀው ከከበደ በረሃ መጥተው ያረፉባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?
ፖለቲከኞች ጎራ ለይተው የማይቧቀሱባት፣ የብሔር ጣዖት የማይመለክባት፣ ሀገርና የሀገር ፍቅር ከፍ ከፍ የሚልባት፣ አንድነት የሚሰበክባት፣ ፍቅር ካባውን የሚያለብሳት፣ ሰላም ከዳር ዳር የሚንሰራፋባት ኢትዮጵያ የት ናት?
ከቀደሙት የቀደመችው፣ ከተወደዱት የተወደደችው፣ ብዙዎች ሳይሰለጥኑ የሰለጠነችው፣ ብዙዎች በጨለማ ውስጥ በነበሩበት ዘመን በስልጣኔ ያበበችው፣ የነጻነት ምሳሌ የሆነችው፣ በጠላቶቿ ፊት ግርማን የተላበሰችው፣ ለየትኛውም ጠላት ያልተገዛችው፣ የራሷን ታሪክ በራሷ ፊደል፣ በራሷ ቀለም፣ በራሷ ብራና ላይ ያሠፈረችው፣ ጥበብ እያፈለቀች፣ እውቀት እንደ ዥረት እያፈሰሰች ትውልድ ያስተማረችው፣ ዳር ድንብሯን በክንዷ ጥንካሬ አስከብራ የኖረችው፣ ከውጭ የመጣን ጠላት ልኩን እያሳየች የመለሰችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የብሔር ፖለቲካ ለክፏት መከራዋን አብዝቶባታል፡፡
ክብሯና ልኳ አንድነት፣ ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አሸናፊነት፣ አርቆ አሳቢነት ሆኖ ሳለ ዛሬ ላይ በብሔር እየለኳት መከራዋን የሚያጠኑባት፣ ከክብሯ ሊያወርዱ የሚጎትቷት በዝተዋል፡፡
ቢሻው በደቡብ፣ ቢፈልጉ በሰሜን፣ ቢያሰኛቸው በምዕራብ እንዲያም ሲል በምሥራቅ ያለስጋት በፍቅርና በክብር ይኖሩባት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ ወሰን ተበጅቶላቸው በአሻቸው አልኖርባት አሉ፡፡ በእናታቸው ቤት ተሳዳጆች፣ ተንከልካዮች ሆኑ፡፡ ከዚህ መለስ ያንተ ነው፣ ከዚሕም መለስ የእኔ ነው በሚል ብሒል መከራ ጸንቶባቸው ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አብዝተው የቀደመችዋን፣ ሰላምና ፍትሕ ያለባትን ኢትዮጵያን አብዝተው ይሻሉ፡፡
ታላቋ ኢትዮጵያ ዓመታትን የዘለቀ ፈተና በዝቶባታል፣ ዓመታትን የተሻገረ ችግር አጉብጧታል፣ ዓመታትን የቆዬ እኩይና አሳናሽ መንፈስ መከራዋን አጽንቶባታል፡፡ ያቺ ፍትሕና ሰላም ያለባት፣ እውነተኞች የሚኖሩባት፣ ስለ ፍትሕ እና ስለ እውነት የሚሠራባት ኢትዮጵያ ተናፍቃለች፡፡ ያዘኑላት መስለው የሚገፏትን፣ የሰሟት መስለው የሚነክሷትን፣ የደገፏት መስለው ምርኩዟን የሚነጥቋትን፣ ያበሩላት መስለው ብርሃኗን የሚነጥቋትን አትሻቸውም፡፡ በፍትሕ ኗሪ፣ ለፍትሕ እና ለእውነት በአደባባይ ተከራካሪ ናትና ያን ትፈልጋለች፡፡
ሕጻናት የማያለቅሱባት፣ እናቶች የማይሳደዱባት፣ በአድማሷ ሥር ከዚህ ውጣልኝ የማይባልባት ኢትዮጵያ ታስፈልጋለች፡፡ በልኳ ትኖር ዘንድ ግድ ይላል፡፡
ነብዩ ፍትሕ ያለባት ያሏትን ኢትዮጵያን እንዴት ነው መመለስ የሚቻለው? ብየ የጠየኳቸው የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ዑዝታዝ በድሩ ሀሴን ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመካ ሃይማኖታቸውን እንደአሻቸው ማራመድ ባልቻሉ ጊዜ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው ነበር፡፡ የላኳቸው ሰዎችም እጅግ ትልልቅ ሰዎች ነበሩ ነው ያሉኝ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከላኳቸው ሰዎች መካከል የእስልምናን ሃይማኖት በሦስተኛነት ከመሩ ሰዎች አንደኛውን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ሰዎች መጥተዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በዚያ ዘመን ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ኢትዮጵያን መርጠዋል፡፡ በዚያም ዘመን አልነጃሺ ነግሰዋል፡፡ ነብዩ ዋናው የመረጡበት ነገር ፍትሕ ነውም ብለውኛል፡፡ ነብዩ በዚያ ዘመን ʺ እሱ ዘንድ ማንም ሰው የማይበደልባት ሀገር ሂዱ” ማለታቸውንም ነግረውኛል፡፡ ፍትሕ አልነጃሺ ጋር እንደሚገኝ እርግጠኛ ሆነው ነው የላኳቸው፣ የሆነውም ያ ነው፤ ሁኔታዎች እስከሚመቻቹላቸው ድረስ በነጻነት ኖረዋልም ነው ያሉኝ፡፡
ፍትሕ ለአንድ ሀገር ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ ፍትሕ የሚመጣው ለተለያዩ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ማንነቶች ልባዊ እውቅና መስጠት ሲቻል ነው፤ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ በታሪክ የተፈጸሙ ሥህተቶች እንዳይደገሙ፣ በታሪክ የታዩ በጎና የሚያኮሩ ተግባራት እንዲቀጥሉ ማድረግ ሲቻል እንደሆነም ነግረውኛል፡፡
ታሪክ ላይ የተፈጠሩ ጉዳዮች በመልካምነትም የሚያሸልሙን አይደሉም፣ በክፋትም የሚያስወቅሱን አይደሉም፤ የምንሸለመውም፣ የምንወቀሰውም እኛው በሠራነው ሥራ ነውም ብለውኛል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ነገሮች ይታኙኛል፣ ጭፍን ጥላቻና ጭፍን ፍቅር፣ እነዚህን ሁለት ነገሮች ማስታረቅ ያስፈልጋል፣ ጭፍን ጥላቻው ጥሩ ነገርን እንዳናይ ያደርገናል፣ ጭፍን ፍቅሩም የተሳሳቱ ነገሮችን እንዳናይ ያደርገናል ነው ያሉት፡፡ ሀገር ለመገንባት ከግለሰቦች ጀምሮ ሁሉም ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ሰው የሚኖረው ሃሳቡን ነው፣ ሀሳባችን ጥሩ ከሆነ ኑሯችን እና ተግባራችን ጥሩ ይሆናል፣ ሃሳባችን ጥሩ ካልሆነ ተግባራችንም ጥሩ አይሆንም፣ ሰዎች በውስጣቸው ያለውን አስተሳሰብ እስካልቀየሩ ድረስ፣ ውጭ ያለውን ሁኔታ አላህ አይቀይርላቸውም፣ ውጭ ያለው ሁኔታ የሚቀየረው ውስጥ ያለው ሁኔታችን ሲስተካከል ነው፣ እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ ለመቀየር እይታችንን ማስተካከል ያስፈልጋልም ብለውኛል፡፡
ከነጋሺ ታሪክ ብዙ ነገር መማር እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ ነጋሺን አስቀድመው በስጦታና ሊያሳስቷቸው የነበሩ እንደነበሩና የነብዩ መልእከተኞች እውነታውን ሲነግሯቸው ማዘናቸውን፣ እውነታውን ሲያውቁም፣ ሊያሳስቷቸው የነበረውን ስጦታህን ይዘህ ሂድ እነዚህን ሰዎች አሳልፌ አልሰጥም፣ በሀገሬ እንደፈለጋችሁ እያመለካችሁ መኖር ትችላላችሁ ያሉ ናቸውም ብለውኛል፡፡
በሌላው ጫማ ቆሞ ማዬት እና እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ነኝ ከማለት መውጣት፣ ካለንበት ሁኔታ እንወጣለን ነው ያሉት፡፡ አላህ ሁሉን ነገር ያደርግልናል፣ እኛ ደግሞ እንደ ሰው ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡
ሃይማኖት የሚለውን እየኖርን ነው ወይ? የሃይማኖት መምህራን ምን ያክል አርዓያ ነን? የሚለውን ማየት አለብን፣ መምህራን አርአያና ቁጥብ መሆን አለባቸውም ነው ያሉት፡፡ ንግግሮች የተቆጠቡ መሆን አለባቸው፣ ነገ ሌሎችን የሚጎዱ መሆን የለባቸውም ብለውኛል፡፡ መነጋርና ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል፣ ስንነጋገር መፍትሔ ይፈልቃልም፣ የምትፈለገዋን ኢትዮጵያ ማምጣት እንችላለን ነው ያሉት፡፡ መነጋገር እና መመካከር፣ አንደኛው በሌላኛው ቦታ ሆኖ ማየት እና ችግሩን መረዳት አሁን ካለንበት ሁኔታ ያወጣናልም ብለዋል።
ፍትሕ ይጸናባት፣ ሰላም ያንዣብብባት፣ ተድላና ደስታ ከዳር ዳር ይሞላባት፣ አንድነት ይጠነክርባት፣ ኢትዮጵያዊነት ይገዝፍባት፣ የሀገር ፍቅር በልብ ውስጥ ይሠርጽባት ዘንድ ሁሉም በቀና ልቡ ይሥራላት፡፡ ያን ጊዜ ፍትሕ ይመጣል፣ ሁሉም መልካም ይሆናል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሮመዷን የነበረው የሰላም፣ የአንድነት፣ የእዝነትና የመረዳዳት ምግባር በቀጣይም ሊተገበር እንደሚገባ የደብረታቦር ከተማ ሙስሊሞች ተናገሩ፡፡
Next articleልጅነት እና የዒድ አልፈጥር በዓል!