በሮመዷን የነበረው የሰላም፣ የአንድነት፣ የእዝነትና የመረዳዳት ምግባር በቀጣይም ሊተገበር እንደሚገባ የደብረታቦር ከተማ ሙስሊሞች ተናገሩ፡፡

65

ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 444ተኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል ፈጥር በዓል በደብረታቦር ከተማ የሶላት ስግደትና በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ተከብሯል፡፡
በረመዷን ወር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ኸይር የሚሠራት፣ በአንድነትና በፍቅር የሚጾምና የሚጸለይበት ነው፡፡ በዘንድሮው የሮመዷን ወርም እንደሁልጊዜው ሙስሊሙ ስለሰው ልጆች ሠላምና ፍቅር ወደ ፈጣሪው አሏህ የጸለየበትና የተቸገሩትን እየረዳ ለታመሙት ምህረትን የለመነበት ሆኖ አልፏል፡፡
የዚሁ የእዝነት፣ የፍቅርና፣ የመረዳዳት ወር ማጠናቀቂያ የሆነው የኢድ አል ፈጥር በዓል በደብረታቦር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ አደባባይ በሶላት፣ ስግደትና ሐይማኖታዊ አስተምህሮ ተከብሯል፡፡
በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ የተሳተፉ ሙስሊሞች ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት፤ የረመዷንን ጾም በመረዳዳትና በመፈቃቀር እንዲሁም ችግረኞችን በመርዳት እንዳሳለፉ ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ የኢድ አል ፈጥር በዓሉም በተክቢራና ሶላት መከበሩንና በረመዷን ወር የሚተገበረው የጾም፣ የጸሎት፣ የእዝነትና የመረዳዳት ሃይማኖታዊ ተግባር በቀጣይ ጊዜም መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡
በበዓሉ ሃይማኖታዊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በደብረታቦር ከተማ ከሚኖረው ሙስሊም ኅብረተሰብ አኳያ ያለው አንድ መስጊድ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ የመስጊድ መገንቢያ ቦታ ጥያቄን ከተማ አሥተዳደሩ እንዲመልስ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
እስላም ሠላም ነው ያሉት የዕለቱ የክብር እንግዳ፤ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ማርየ በለጠ (ዶ.ር) ለደብረታቦር ከተማ ሠላምና ልማት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ አስፈላጊነት ጠቅሰው ለኅብረተሰቡ ጥያቄ ህጋዊ መፍትሄ ለመሥጠት ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የመስጊዱን ግቢ እና በዓሉ የሚከበርበትን አደባባይ በማጽዳት የክርስትና ሃይማኖት ወጣቶችም የተሳተፉ ሲሆን ላደረጉት የአክብሮት ሥራም ሙስሊሞቹ አመስግነዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዒድ አልፈጥር በዓልን ማንነታችን ተከብሮ በነፃነት እያከበርን ነው ” የአላማጣ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች
Next articleፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ከየት ናት?