በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ የታሰበው ውይይት ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

169

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመወያየት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚቴ ለዛሬ የቀጠረው የሕዝብ አስተያየየት መስጫ መድረክ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማነስ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው መድረኩን ለሌላ ጊዜ ያስተላለፈው በሕዝብ ተሳትፎ ረቂቅ አዋጁ ቢጸድቅ ለቋሚ ኮሚቴው የላቀ እርካታ እንደሚሰጥ በማመንና ጉዳዩም የብዙ ወገኖች ተሳትፎ ቢኖርበት የበለጠ ስሚጎለብት የግድ ሰፊ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ በማመን ነው፡፡
ለውይይቱ ከ15 ተቋማት በላይ በደብዳቤ መጋበዛቸውንና በመገናኛ ብዙኃንም ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ማስታወቂያ በሬዲዮና በቴሌቪዥን መነገሩን ያስታወሰው ቋሚ ኮሚቴው በመድረኩ የተገኙት ብዛት በጣም ዝቅተኛ ሆኖበታል፤ በዚህ የተነሳም ለተፈጠረው መስተጓጎል የተገኙትን ተቋማት ይቅርታ በመጠየቅ ስብሰባው እንዲበተን አድርጓል፡፡ በቀጣይ ችግሩ እንዳይከሰት ማስታወቂያ እንደገና እንዲነገር፤ ጥሪ ቀርቦላቸው የቀሩ ተቋማትም ዳግም ጥሪው እንዲደረግላቸውና የቀሩበትንም ምክንያት የሚያሳውቁበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተመሥገን ባይሳ (ዶክተር) የተሻለ ሕግ እንዲወጣ ዩኒቨርሲቲዎች በጣም ይፈለጉ እንደነበር ጠቁመው በቀጣይ የተሻለ ተሳታፊ በተገኘበት የሕዝብ አስተያዬት መስጫ መድረኩን ማስቀጠል ‘‘ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ያልተወያየበት ሕግ ነው’’ የሚባለውን አስተያዬት ለማስቀረት ሲባል ስብሰባው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ጥሪውን አክብረው በቦታው ለተገኙ ተሳታፊዎች በመግለፅ ስብሰባው እንዲበተን አድርገዋል፡፡

በማረሚያ ቤቶች ይከሰቱ የነበሩ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ታስቦ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ በ1ኛ መደበኛ ስብሰባው መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይቶ ዝርዝር ውይይቶች ተደርጎበት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ሆኖ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ እንደነበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ገጹ አስታውሷል፡፡

Previous articleከ60 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረው ተጨማሪ 28 ሚሊዮን ብር ለማጭበርበር ሂደት ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥ ሥር ዋሉ፡፡
Next articleየብሔራዊ የእንስሳት ጥበቃ ኢንስቲትዩት የተለያዩ ክትባቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት እያቀረበ ነው፤ አበረታች አፈጻጸም ማሳየቱም ተመላክቷል፡፡