“በረመዷን የተፈቀደውን እንዳያደርግ የተከለከለ ከረመዷን በኋላ ያልተፈቀደለትን ነገር መዳፈር አይፈቅድለትም” ኡስታዝ በድሩ ሁሴን

137
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የረመዷን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ ወር ነው። የእስልምና እምነት መሠረቶች ከሆኑት አንዱ የኾነው ጾምና ሰላት የሃይማኖታዊ ግብረ ገብ ማጎልበቻ መንገድ መኾኑን ኡስታዝ በድሩ ነግረውናል። በረመዷን ፆም የእምነቱ ተከታዮች አላህን በመፍራት ከመጥፎ ነገር ራሳቸውን በማቀብ መልካም ነገር እንዲሠሩ ማድረግ እንደኾነም ነው ኡዝታዝ በድሩ የገለጹልን።
የረመዷን ፆም የእምነቱ ተከታዮች አሏህ የማይፈልገውን ነገር እንዲጸየፉ ውስጣዊ ባሕሪን መግሪያም መንገድ ነው። ውስጣዊ ባሕሪው የተገራ ምዕመን ደግሞ ውጫዊ ባሕሪውን ከመጥፎ ነገር እንዲያርቅና መልካም ነገርን እንዲከውን ያደርገዋል። ውስጥን ማጽዳት ሲቻል እንደ ግለሰብ ብሎም እንደ ሀገር ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጎልበት ያግዛል።
“በረመዷን ፆም የተፈቀደ ነገር የተከለከለ ነው። በረመዷን ወር የተፈቀደውን የተከለከለ የእምነቱ ተከታይ ከረመዷን በኋላ ያልተፈቀደለትን ነገር መዳፈር ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባሩ አይፈቅድለትም” ብለዋል ኡስታዝ በድሩ። ለተቸገሩት ዘካ መስጠትና አቅመ ደካሞችን መርዳት ደግሞ ሌላኛው ሃይማኖታዊ መሠረት እንደኾነ ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የነብዩ ሙሐመድን ልግስና በማሳያነት ጠቅሰዋል። ኡስታዝ በድሩ እንዳሉት ነብዩ ሙሐመድ ምጽዋት ለምንዱባን ስለሚያከፋፍሉ ከሦስት ቀን በላይ ገንዘብ አያስቀምጡም። ሁሌም ለጋስ ቢኾኑም በረመዷን ደግሞ ልግስናቸው የተለየ እንደነበር ገልጸዋል። “ነብያት ለሕዝባቸው እምነትን እንጅ ገንዘብን አያወርሱም” እንዳሉም ነግረውናል።
በረመዷን የሚከናወኑ መልካም ሃይማኖታዊ እሴቶች እና አስተምሕሮዎች ሁሉ ከረመዷን በኋላ ባሉት አስራ አንድ ወራትም አማኞች ራሳቸውን ለመግዛት፣ ለማነጽና ለማረቅ የሚተገብሩት በመኾኑ የረመዷን ወር በሙስሊሙ ልሂቃን እንደ ስልጠና ማዕከል ተደርጎ እንደሚታይ ነው ኡስታዝ በድሩ የነገሩን።
በመኾኑም ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን ለማጎልበት በረመዷን በተለየ መልኩ የተሰጠውን አስተምሕሮ በሌሎች ወራትም አርብ ቀን በመስጅዶች፣ በዒድ አልፈጥርና በአረፋ ከፍ ሲል ደግሞ እንደ ዓለም በሃጂ በዓላት ላይ በመሰባሰብ ሃይማኖታዊ የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራ ዓመቱን ሙሉ ይከናወናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺአላህ የመረጣቸው፣ ትህትና የተቸራቸው”
Next article“የዒድ አልፈጥር በዓልን ማንነታችን ተከብሮ በነፃነት እያከበርን ነው ” የአላማጣ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች