
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፈጣሪ መረጣቸው፣ መልዕክተኛው አድርጎ ላካቸው፣ የመጨረሻው ነቢይ አድርጎ ሾማቸው፡፡ ትሕትና ተችሯቸዋል፣ ጥበብ እና መልካምነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አብዝተው ያዝናሉ፣ ርህራሄን ያደርጋሉ፣ መልካምነትን ያስተምራሉ፡፡
ሐሩር የሚበዛባት፣ የፀሐይ ወበቅ የሚጠናባት፣ አፍላጋት እንደፈለጉ የማይፈስሱባት፣ ሐይቆች እና ባሕሮች እንዳሻቸው በማይገኙባት፣ አሥፈሪ በረሃዎች በበዙባት በዚያች ምድር ፍትሕ ተጥሳባት፣ ጣዖት አምላኪዎች በርክተውባት፣ ክፉ የሚያደርጉ በዝተውባትም ነበር፡፡
ኀያላን ነገሥታት በተዋበ ቤተ መንግሥት በአጀብ ይኖሩባታል፣ አስፈሪ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የቤተ መንግሥት አሽከሮች ያጅቧቸዋል፣ የሚሹትን ያደርጉላቸዋል፤ በአማሩ ጎዳናዎች፣ በተዋቡ ሠረገላዎች በታላቅ አጀብ ይመላለሳሉ፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ በግርማ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ፣ ወገናቸው ከነገሥታቱ፣ ከመኳንንቱና ከመሳፍንቱ የሆኑ ሁሉ ተድላና ደስታ አላቸው፡፡ ከነገሥታት ወገን ያልሆኑት በዚያች በረሃማ ምድር የሚኖሩት ግን የተድላ ሕይወትን አያውቁም ነበር ይባላል፡፡
በዚያች ምድር የአላህ አምላክነት ተዘንግቶ፣ ምድር መከራ በዝቶባት፤ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ርቆ ነበር፡፡ በጣዖት አምልኮ ሰዎች ተዘፍቀዋል፤ ነገሥታቱ እንዳሻቸው የሚሆኑባት፣ ሴቶች የሚንገላቱባት፣ ድሆች በመከራ የሚኖሩባት፣ ሀብታሞች በድሎት የሚንፈላሰሱባት፣ እኩልነት እና ፍትሕ የራቀባት ኾናም ነበር ይላሉ፡፡
ይህን ያየው አላህም የመረጣቸውን መልዕክተኛ በዚያች ምድር ላከ፡፡ ያቺም ምድር የአረቡ ዓለም የምትባለው ናት፡፡ መነሻቸው በአረቡ ዓለም ይሁን እንጂ አስተምህሯቸው እና ተልእኮዓቸው ግን ለዓለም ነው፡፡ የአላህ መልዕክተኛም በመካ ተወለዱ፡፡ እኝህ የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ናቸው፡፡ አስቀድመው ለታላቅ ዓላማ ታጭተዋልና ያስተውላሉ፣ መልካም ነገርን ያደርጋሉ፣ አብዝተው ይታመናሉ፡፡
ከጣዖት አምላኪዎች ጋር አልተባበሩም፣ የዚያ ዘመን ወጣቶች ያደርጉት እንደነበር አስካሪ መጠጦችን አልጠጡም፣ ከክፉ ሥራዎች ጋር አልተዋወቁም፣ ከክፉ ሥሪዎች ጋርም አልተባበሩም፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ወጣቶች ይውሉባቸው ከነበሩ ክፉ ሥራዎች አልዋሉም፡፡ ከክፉ ሥራዎች ይርቃሉ፣ ነገሮችን በብስለት ይመረምራሉ፣ ዕውቀትንም ይገበያሉ ይሏቸዋል፡፡
የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአላህ ትዕዛዝ እና መልእክት አማካኝነት ክፉ ሥራ ለበዛበት ምድር መልካም ነገር አመጡላት፡፡ ጣዖታትን እንዲወድቁና እንዲናቁ አላህ ብቻ እንዲመለክ አደረጉ፡፡ ሰዎች ሁሉ ያለምንም ልዩነት እኩል መሆናቸውን አስተማሩ፣ መብት ይከበር ዘንድ ሠሩ፡፡ ይህንም ሲያስተምሩ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ ፈተናዎች በዝተውባቸው፣ መከራዎች ጸንተውባቸው ነበር እንጂ፡፡ እሳቸው ግን በችግሮች አልተደናቀፉም፣ ወደ ኋላም አላሉም፣ በትዕግስት እና በጽናት አላህ ያደርጉ ዘንድ ያዘዛቸውን አደረጉ እንጂ፡፡
ስለ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጠቢባን ይናገሩላቸዋል፣ ይጽፉላቸዋል፣ ነገር ግን ከሰብዕናቸው ጥቂቱን ይናገራሉ እንጂ አይዘልቁትም፣ ስለ እሳቸው ሁሉንም መናገር አይችሉትም ይሏቸዋል፡፡ እርሳቸው በሁሉም ሕይወት አርዓያ የሆኑ ናቸውና፣ በቀላሉ ተነግሮላቸው፣ ተጽፎላቸውና ተመስክሮላቸው አይዘለቅም ይባላል፡፡ ልጅ ሆነው ሲታዘዙ፣ አባወራ ሆነው ቤት ሲመሩ፣ የጦር መሪ ሆነው ጦረኛ ሲያሰማሩ፣ የመስጂድ ኢማም ሆነው ሲያሰግዱ፣ ሃይማኖትን ሲያስተምሩ፣ ሀገርንም ሲያስተዳድሩ የተሳካላቸው በሁሉም የሕይወት ዘርፍ አርዓያ የሆኑ ነቢይ ናቸው፡፡
እዝነታቸው ወሰን የለውም፤ ሁሉንም ፍጥረታትን ያዳረሰ ነው፣ ሚዛናዊነታቸው ግሩም ድንቅ ነው፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ከስጋዊ ሕይወት ጋር በሚዛን እንዴት መምራት እንደሚቻል አርዓያ ሆነውም ያስተማሩ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ አባቶች ነቢዩ ሙሐመድ ለሁሉም የሰው ዘር የሚሆን አስተምዕሮና አርዓያነት አስተምረውናልም ይላሉ፡፡
በዓለማት ላይ መተዛዘን እና ርህራሄ እንዲሰፍን የተላኩ ነቢይ ናቸው፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ወደ ምድር የመጡት እዝነትና ሩህሩህነት እንዲኖር መሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡ እርሳቸው የታላቅ ሥነ ምግባር ባለቤት ናቸው፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል የነቢዩ ሙሐመድን አስተምህሮ ከተገበርን ዓለሙ ሁሉ ሰላም ይሆናል ይላሉ፡፡ እርሳቸው ሰላምን አብዝተው የሚሹ አስተምህሯቸው እና አርዓያናታቸው ሰላም የሆነ ነውና፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባላዘነች ምድር መጥተው አዘኑ፣ እዝነትንም አስተማሩ፣ እርሳቸው ዓለም ከጭንቅ የዳነችባቸው ነቢይ ናቸው፡፡አላህ ሲመርጣቸው አርዓያ እንዲሆኑ አድርጎ ነው ይሏቸዋል ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡ በባሕሪያቸው፣ በሥራቸው በሁሉም ተግባራቸው አርዓያ እንዲሆኑ አድርጎ የፈጠራቸው ናቸው ነው የሚሏቸው፡፡ እርሳቸው የትኛው ሰው ለየትኛው ተግባር እንደሚሆን የሚያውቁ እና ለሁሉም ባለቤት የሚሰጡ ጥበበኛ መሪም ናቸው፡፡
እርሳቸውን ያስተማራቸው መልዓኩ ጅብሪል ነበር፣ ከአንደበቶቻቸው የሚወጡ ቃላት ይማርካሉ፣ ቀልብ ይስባሉ፣ ለጀሮ ይስማማሉ፣ ለልቡና ሀሴትን ይሰጣሉ፣ ስሙኝ ስሙኝ፣ አድምጡኝ አድምጡኝ ያስብላል ነው ያሉኝ፡፡ እርሳቸው ማስተዋልን የተቸራቸው እንደሆኑም ነግረውኛል፡፡
በትዕግሥት አላህ የሰጣቸውን መልዕክት ለዓለም አድርሰዋል፣ በትዕግሥትና በጥበብ ቁጥራቸው የበዛ ተከታዮችን አፍርተዋል፡፡ ፈተና በበዛባት ምድር የአላህን ትክክለኛ መልዕክት ለሕዝብ አድርሰዋል፣ በዓለም ዙሪያ ይዳረስ ዘንድም አድርገዋል ነው የሚሏቸው፡፡ የእምነቱ ተከታይ ያልሆነ ሰው ጥገኝነት ቢጠይቅ ተቀብለው፣ ጥበቃ እንዲደረግለት የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፡፡
ነቢዩ ለሰው ልጅ የሚበጁ አስተምህሮዎችን ሁሉ አስተምረዋል፣ ይመራባቸው ዘንድም አስቀምጠዋል፡፡ ʺወላሂ ጎረቤቱን የማያምን፣ ከጎረቤቱ ጋር የማይተማመን አማኝ አይባልም” ማለታቸውንም ፕሮፌሰር አደም ነግረውኛል፡፡ ምግብ ስትሠራ አካፍለህ ስጥ እንጂ ብቻህን አትብላ የሚሉ፣ ሰላም፣ ትብብር፣ መከባበር እንዲኖር ያስተማሩ ናቸውም ነው ያሉት፡፡
የነቢዩ መሐመድን አስተምህሮ ከተገበርን በእርግጠኝነት ዓለማችን በሰላም ትኖራለችም ብለውኛል ፕሮፌሰሩ፡፡ እርሳቸው በዘመናቸው የበዙ ፈተናዎች እና መከራዎች ደርሰውባቸዋል፣ በመቻል፣ በትዕግሥት አልፈዋቸዋል ብለውኛል፡፡
የአሁኗ ዓለም የነብዩን አዛኝነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ፍትሐዊነት፣ የሰላም ሰባኪነት፣ አንድነት እና ትዕግስትን ትሻለች፡፡ የእርሳቸውን ባሕሪ የተላበሰ፣ እርሳቸውንም አርዓያ ያደረገ ካለ ዓለም አትራቆትም፣ አትራብም፣ በጦርነት አትጎሳቆልም፣ ጎራ ከፍላ አትታኮስም፣ ወገንን ከወገኑ ጋር አታጋድልም መከራዋም አይበዛም ይላሉ፡፡ አላህ የመረጣቸው፣ ትህትናም የበዛላቸው፣ ጥበብም የተቸራቸው ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለምድር ታላቅ ነገርን አድርገዋል፡፡
መልካምነትን ከመልካሞች ተማሩ፣ በመልካምነትም ኑሩ፡፡ መልካም ማድረግ መልካም ነገርን ይከፍላልና፡፡
በታርቆ ክንዴ