“ሀገራችን ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገር የፍቅርና የመቻቻል መንገድ መከተል ይኖርብናል” አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

283
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፣ ኢትዮጵያውያን ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ቀናይነት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል፣ በይቅር ባይነት አልፈው ሀገራቸውን አጽንተው ለማቆየት መቻላቸውን አውስተዋል።
በዚህ የረመዳን ቅዱስ ወር የጀነት (የገነት) በሮች የሚከፈቱበት፣ የጀሃነም (የገሃነም) በሮች የሚዘጉበት፣ ሠይጣንም የሚታሰርበት፣ መልካምነት ጎልቶ የሚሠፍንበት፣ የፈጣሪ ምሕረት የሚበዛበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ረመዷን ክፉ ማሰብና ክፉ ማድረግ ቀርቶ የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ወር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የወሩ ፍጻሜ እና የጾም ፍቺ የሆነችው ዒድ አልፈጥር ደግሞ የበጎ ነገሮች ሁሉ ማሠሪያ ተደርጋ ትወሰዳለችም ነው ያሉት።
የእምነቱ ተከታዮች በዒድ አልፈጥር በዓል ለተቸገሩት ዘካን በማውጣት፣ እንዲሁም ምስኪኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ለተቸገሩት ዘካትል ፊጥር (ምጽዋት) በመስጠት፣ የደከመን በመደገፍ የሚያሳልፉት ከፈጣሪ ምሕረትንና ጽድቅን ለማግኘት ነው ብለዋል።
ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገርም አባቶቻችን ችግሮቻቸውን ሲፈቱበት የቆየውን የፍቅርና የመቻቻል መንገድ መከተል ይኖርብናልም ነው ያሉት።
ሁላችንም የእምነቶቻችን አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት መጓዝ ከቻልን የከበደው ይቀላል፣ የጨለመው ይበራል፣ ውስብስቡና ውል ያጣው ችግራችን ሁሉ መፍትሔ ያገኛልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር በተለያዩ ሀገራት።
Next article“ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት