ዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር በተለያዩ ሀገራት።

266

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢድ አል ፈጥር በታላቁ የረመዷን ወር መጨረሻ ላይ የሚከበር የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓል ነው። በዓሉ በሀገራችን ኢትዮጵያ በድምቀት ይከበራል። የእምነቱ ተከታዮች ወደ አደባባይ በመውጣት የኢድ ሶላትን በጋራ ይሰግዳሉ። ለረመዷን በሰላም መጠናቀቅ አላህን ያመሰግናሉ። በቀጣይ ዓመት በሰላም ለመድረስም ዱዓ ይደረጋል። ያለው ለሌለው ማካፈል እና ቀኑን በደስታ እና በጋራ ማሳለፍ ዋነኛ የበዓሉ መልክ ነው።

በዓሉ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ የዓለም ሀገራት በተለያየ ድምቀት ይከበራል። የኢድ አል ፈጥር ወቅት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የዓመቱ ትልቅ ገበያ የሚገበይበት ነው። ከምግብ ሸቀጥ ጀምሮ የአልባሳት እና የሌሎች ቁሳቁሶች ገበያ ይደራል።

በበዓሉ ዋዜማ የሶማሊያ ሴቶች ፋሽን ልብሶችን ይገዛሉ፤ የመዋቢያ ቁሳቁስ እና የሽቶ ገበያው የበለጠ ይጧጧፋል። በዕለቱ በመስኪዶች ከሚደረገው የኢድ ሶላት መልስ ዋነኛው የበዓል አከባበር ይጀመራል። በየቤቱ የተዘጋጁ ለሆህ፣ ባጊያ፣ ሃኒድ እና የመሳሰሉ የምግብ ዓይነቶችን ሁሉም በጋራ ይመገባል። በዚህ ማዕድ ለመካፈል ዝምድና ወይም መተዋወቅ አይጠይቅም። እግሩ ያደረሰው እንግዳ ሁሉ የማዕዱ ተጋሪ ነው። ከቀማመሰ በኋላም “ኢድ ዋናክሰን” ብሎ ይሰነባበታል። መልካም በዓል ማለቱ ነው።

ሌላዋ አፍሪካዊት ሀገር ሞሮኮም ኢድ አል ፈጥርን በድምቀት ታከብራለች። በሞሮኮ የበዓሉ ቀን ጥዋት ሁሉም ወንዶች ወደ መስኪድ ይሄዱና የኢድ ሶላት ይሰግዳሉ። ሴቶች ደግሞ በቤታቸው ኾነው “መለዌ” እና “ባህንጋህሪ” የተባሉ ጣፋጭ ባሕላዊ ምግቦችን ያሰናዳሉ። ወንዶች ከመስኪድ እንደተመለሱ የተዘጋጀውን ይመገባሉ።
ከዚህ በመቀጠል ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መጠያየቅ በሞሮኮ የተለመደ ነው። የኢድ ቀን በሞሮኮ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም የተቸገሩ አካላት ይጠየቃሉ። የታመሙትን በሆስፒታል እየተገኙ መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘት፣ በድህነት ውስጥ ያሉትን ማብላት፣ የተከፋትን ማስደሰት የሞሮካዊያን የኢድ አል ፈጥር በዓል ዋነኛ ተግባር ነው።

ኢድ አል ፈጥርን በፓኪስታን በተለይም ሴቶች በሂና መድመቃቸው ልዩ ያደርገዋል። ሂና ሴቶች በእጅና በእግሮቻቸው ላይ በደማቁ እና በተለያየ ቅርጽ የሚቀቡት መዋቢያ ነው። ሂና በፓኪስታኖች በስፋት ይለመድ እንጅ በተለያዩ ሀገሮች ጥቅም ላይ የሚውል መዋቢያ ነው።

በኢድ አል ፈጥር ጥዋት ሁሉም የፓኪስታን ወንዶች ወደ መስኪድ ይሄዱና በዚያው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። ጸሎቱ እንደተጠናቀቀ ወጣቶች ስጋ ለማረድ ዝግጁ ኾነው በመስኪዱ ዙሪያ ይጠባበቃሉ። ወዲያውኑ የእርድ እንስሳትን በግል ወይም በቡድን ያዘጋጁ ሰዎች ወደ መስኪዱ ያመጣሉ። የተዘጋጁ ወጣቶች እርዱን አከናውነው ሁሉንም ካዘጋጁ በኋላ በዚያ ሰፈር የሚገኙ አቅመ ደካሞች ጭምር ተሰብስበው በጋራ ይመገባሉ። መምጣት ላልቻለው ደግሞ እየተቋጠረ ይላክለታል። ከምግብ በኋላ በሂና የተዋቡ የፓኪስታን ሴቶች በመዘዋወር “ኢድ ሙባረክ” እያሉ በዓሉን ያደምቃሉ።

ኢድ ሙባረክ! ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም በዓል!
አልጀዚራ፣ ሮይተርስ እና ሙስሊም ቻናልስ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዒድ አልፈጥር በዓል ሲከበር የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ ሊኾን እንደሚገባ ፖሊስ አሳሰበ።
Next article“ሀገራችን ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገር የፍቅርና የመቻቻል መንገድ መከተል ይኖርብናል” አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር