
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓላትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ተገማች ችግሮች መኖራቸውን ያስታወሰው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በዓሉ በሰላም እንዲያልፍ ሰዎች ለአካባቢያቸው ሰላም ቅድሚያ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
ስርቆት፣ ማጭበርበር፣ የትራፊክና የእሳት አደጋ፣ በሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ግብይት መፈጸም በተለያዩ በዓላት ወቅት የሚከሰቱ የወንጀል ድርጊቶችና አደጋዎች መኾናቸውን ነው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ የገለጹት።
ከዒድ አልፈጥር በዓል በፊት በተከበሩ በዓላት ዋዜማ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው መጠን በላይ ጭነው ሲያሽከረክሩ በደረሰው አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም በማሳያነት አንስተዋል።
ማኅበረሰቡም በዒድ አልፈጥር በዓል ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን እና ትርፍ በመጫንና ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ምክንያት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ መከላከል እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት።
የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወጣቶች የክርስትና እምነት በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ያነሱት ኮማንደሩ የዒድ አልፈጥር በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ የክርስትና እምነት ተከታይ ወጣቶች ከፖሊስ ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!