እሙ አይመን – የጀነት ሴት!

129
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዘር ሀረጓ በዘመኑ ስደት እና ባርነት ከሀገራቸው ገፍቶ ካስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ይመዘዛል፡፡ እንዴት እና በምን ሁኔታ ለአስከፊው የባርነት ሕይዎት እንደተጋለጠች በውል ባይታዎቅም በዚያ የጨለማ ሕይዎት ውስጥ አልፋ ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀች ጽኑ፣ ታማኝ፣ ተወዳጅ እና የጀነት ሴት እንደነበረች ግን የሕይዎት ታሪኳ ያስረዳል፡፡
መካ የእስልምና ሃይማኖትን ስትከለክል እና የእምነቱ ተከታዮች ሲሳደዱ ሁለት ጊዜ ሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱት መካከል ይኽች ሴት ትገኛለች፡፡ ከሀገሯ በባርነት የወጣች፤ ስላሃይማኖቷ ደግሞ ወደ ሀገሯ መልሳ እና መላልሳ የተሳደደች ጽኑ እና ብርቱ እናት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ እንደ ቢላልም እንደ አልነጃሽም ኢትዮጵያን እና እስልምናን በጽኑ መሰረት ካቆራኙት ሰዎች መካከል ይኽች ሴት ተጠቃሽ ናት፡፡
ቤተሰቦቿ ያወጡላት እና የልጅነት መጠሪያ ስሟ በረካ አል ሐበሽ ይባላል፡፡ እሙ አይመን ወይም የአይመን እናት ደግሞ እንደ አረቦቹ ባህል በመጀመሪያ ልጇ ስትጠራ ነው፡፡ እሙ አይመን በረካ ወይም የአይመን እናት የአሏህን መልዕክተኛ በእምነት ተቀብላ በጽናት ያሳደገች የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለተኛ እናት ናት፡፡ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልጅነት ዘመናቸው ሞግዚት እና የወጣትነት ዘመናቸው እህት ናት፡፡ ሃይማኖቷን አጥባቂ እና ነብዩን ጠባቂ በመሆኗ በብዙዎች ዘንድ አብዝታ ትወደድ ነበር ይባላል፡፡
እሙ አይመን በረካ ከብዙ ሴቶች በብዙው ትለያለች ያሉን የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ መምህር የሆኑት ሼክ ሀሰን ገላው ናቸው፡፡ መምህሩ እሙ አይመንን ሲገልጿትም ይኽች ሴት ከብዙዎች መካከል ተለይታ በመከራ የጸናች፣ በቃሏ የተገኘች፣ በአሏህ ፍቅር የተገራች እና ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር እስከ ሕይዎት ዘመን ፍጻሜ ከጎናቸው ያልተለየች ሴት ነች፡፡
ይኽች ሴት በአሏህ መልዕክተኛ “የጀነት ሴት” ተብላ የተጠራች ብርቱ እና ታታሪ ሴት ነች፡፡ ይኽች ሴት በምድር የተቀበለችውን አደራ በሰማይ የመለሰች፤ ላመነችበት እውነት ሞትን ሳትፈራ እና ለራሷ ሳትራራ በመከራ መካከል ደጋግማ የተመላለሰች ብርቱ ሴት ነበረች ይላሉ፡፡
እሙ አይመን በረካ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወላጅ እናት አሚናን በመከራዋ ዘመን ከጎኗ ሆና ያበረታች፣ በእርግዝናዋ ወቅት ለአፍታ ሳትለይ የተንከባከበች፣ ስትወልድ በቅርብ የተገኘች እና ያረሰች እድለኛ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት ይላሉ መምህሩ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይኽችን ምድር ሲቀላቀሉ በቅድሚያ ያረፉት በእሙ አይመን ክንድ ላይ ነበር፡፡ የነብዩን እናት አሚናን ብቻዋን አልቅሳ የቀበረች፤ ልጇን ነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ተቀብላ ያሳደገች እና በ63 ዓመታቸው በሞት ሲለዩ አምርራ ያዘነች የመከራ ዘመን ጽናት፤ የፈተና ዘመን ብርታት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች ይሏታል፡፡
የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ “አብዛሃኛውን ጊዜም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከበረካ አንገት አካባቢ እጃቸውን ተደግፈው ይተኙ ነበር” ይላሉ፡፡ ሼክ ሀሰን እንደሚሉት ነብያችን ከልጅነት እስከ እውቀት፤ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ከሚያውቋቸው እና ከጎናቸው ካልተለዩ ሶኻባያዎቻቸው መካከል እሙ አይመን አንዷ ናት፡፡ ለዚያም ይመስላል ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “እሙ አይመን ከእናቴ በኋላ እናቴ ነሽ” ሲሉ የመሰከሩላቸው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በአንደበታቸው “የጀነት ሴት” ያሏትን እሙ አይመንን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ ከሶኻባዎቻቸው መካከል በጣም ለሚወዱት እና በስማቸው እስከመጠራት ለደረሰው ዘይድ ኢብን አልሐሪሳ ድረዋታል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች እሙ አይመንን እንደ አንድ የእስልምና ሃይማኖት ባለውለታ ስናያት ኢትዮጵያዊ በመሆኗ ብቻ አይደለም የሚሉት ሼክ ሀሰን እስልምና በፈተና፣ በመሳደድ እና በችግር ላይ በነበረበት ወቅት ለቃሏ እና ለሃይማኖቷ ጹኑ ሆና በመገኘቷ ነበር ይላሉ፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ለሃይማኖት መጽናትን፣ ለሀገር መበርታትን፣ ለቃል መገኘትን እና ላመኑበት መሞትን ከእሙ አይመን ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“እንኳን ለዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!” ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ
Next articleየዒድ አልፈጥር በዓል ሲከበር የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ ሊኾን እንደሚገባ ፖሊስ አሳሰበ።