
“እንኳን ለ1444 ኛው የዒድ-አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሣችሁ! ዒድ -ሙባረክ 🕌”የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
አምላክ በፈቃዱ ከፈጠራቸው ሰዎች፤ ቀናቶች፤ ወራቶችና ቦታዎች መካከል መርጦ በሌሎቹ ላይ ልቅናን እና ቅድስናን ይሠጣል፡፡
እንዲሁ ሁሉ የዓለማት ፈጣሪና የግዜ ባለቤት የሆነው አምላክ ከፈጠራቸው ወራቶች መካከል አብዝቶ የቀደሰው ወርሃ ረመዷን ፤ አሏህ (ሱ.ወ) ለሠው ልጆች ሁሉ መመሪያ ይሆን ዘንድ ታላቁን መጽሐፍ ቁርዓንን ያወረደበት፤ ሙዕሚን እና ሙዕሚናት በጾምና በጸሎት ተግተው ከየትኛውም ግዜ በላይ በመልካም ሥነ ምግባር የሚበረቱበት እና ይቅርታና ምሕረትን ሽተው ወደ አምላክ እጆቻቸውን ለሚዘረጉ ጸጸተኞች ሁሉም የጀነት በሮች የሚከፈቱበት ፤የርህራሄ እና የእዝነት ወር ነው፡፡
ይህን የተባረከ ተናፋቂ ወር መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በጾም እና በጸሎት፤ በደግነት፤ በልግስና እና ፍጹም የሆነ መለኮታዊ ታዛዥነትን ተላብሰው በሚፈጽሟቸው በጎ አድራጎቶች ምክንያት ቀዬዓችን ብቻ ሳይሆን ምድሪቱም እንዲሁ በይቅርታ፤ በእርስ በርስ መተዛዘንና የርህራሄ ዘለበት ተሰናስና ስትስተዋል፤ የሠው ልጅ የሕይወቱ ውበትና ሞገስ በራሱ በሠው ልጅ መልካም ስነ ምግባራዊ መስተጋብር ላይ ምን ያህል የተቆራኘ መሆኑን ያስረዳናል፡፡
የሠው ልጅ ከቁስ አካላዊው ዓለም ባሻገር ለሚገኘው በወዲያኛይቱ መንፈሳዊ ሀገሩ ላይ ለሚኖረው ዘለዓለማዊ ሕይወት የከበረ ደረጃ ሲል በዚህችኛይቱ ቅርብ ዓለም በሥጋ ሳለ የሚከውናቸው የይቅርታ፤ የእዝነትና የልግስና ተግባራት ከአጸፋዊ ነጸብራቃቸው የሚያገኘው ውስጣዊ ሠላም ከራሱ፤ ከቤተሰቡ እና ከመኖሪያ ቀዬው አልፎ ለመላው ዜጎችና ለሀገር ይተርፋል፡፡
ሠው እንዲህ ባለው ሠናይ ምግባር ወጥነት ባለው መንገድ ተግቶ መገኘቱ የምልዑ ሰውነት ደረጃው በገሃድ እንዲገለጥ ከማስቻሉ ባሻገር ከግለሰባዊ ሰናይ መስተጋብሩ ድግግሞሽ ሳቢያ ጤናማ ማህበራዊ መስተዋድድ ያለው ጤናማ ማህበረሰብ እንዲበዛ ያደርጋል፡፡ በተቀደሰው የረመዷን ወርም ፋፍተው ከተመለከትናቸው ወርቃማ እሴቶች መካከልም አንዱ ይህ እሴት ነው፡፡
ሥለሆነም በአማራ ክልል የምትገኙ መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ ከተናፋቂው የረመዷን ወር መሰናበት በኋላም ቢሆን በተቀደሰው ወር የተገነባውን ምልዑ ስብእና በመላበስ፤ በማይቋረጥ የበጎነት ተግባራት ላይ በማዘውተር በክልላችን ሁለንተናዊ ሠላም፤ ፍትሐዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር የማይተካ ሚናችሁን እየጠየቅን መልካም የዒድ-አልፈጥር በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኛለን፡። ዒድ ሙባረክ 🕋
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር