
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዒድ አል ፈጥር የረመዳን የጾም ወር መጠናቀቁን አብሳሪ፤ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድም በጉጉት የሚጠብቁት ሃይማኖታዊ በዓል ነው። በዓሉን ሙስሊሞች በመላው ዓለም በድምቀት ይከብሩታል፡፡
በዒድ አልፈጥር በዓል የሚከናወኑ ተግባራትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ ሙሐመድ አንዋር “ዒዱ በሃማኖታዊ ሕግጋትና ትዛዛት ነው ተጀምሮ የሚጠናቀቀው” ይላሉ፡፡
ሸህ ሙሐመድ አንዋር እንደሚያስረዱት የሃይማኖቱ ተከታዩች በሃይማኖቱ አስተምህሮ ከሁሉም አስቀድሞ በዒድ በዓል “ችግረኞችን ማሰብ ” የሚለው ትዕዛዝን ተፈጻሚ ያደርጋሉ፡፡ ይህም “ሰደቀተል ፊጥር” ይባላል ይሉታል፡፡
ትልቅም ይሁን ትንሽ ሴትም ኾነ ወንድ ሳይል የመጀመሪያውን ሰደቀተል ፊጥር ማድረግ እንደሚገባ ነው የሚያስረዱት፡፡
ይህም ሁለት መሰረት እንዳለው ነው ሸህ ሙሐመድ የሚያስረዱት፡፡ አንደኛው በጾም ሰዓት የተፈጸሙ ስህተቶች ማጽጃ ነው፤ሁለተኛው ደግሞ የተቸገሩትን ሁሉ ዒድን (በዓሉን) በደስታ ለማሳለፍ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ችግረኛው ማኅበረሰብ “እኔ ወደ ሶላት ስሄድ ልጆቼ ምን ይበላሉ “ብሎ እንዳያስብ ለማስቻል ነው፡፡
👉የዒድ ሶላት ሥነ ሥርዓት:- ሌላው የዒድ ሥነ ሥርዓት ሶላተል ኢድ ይባላል፡- ኢድ ተክቢራን እየተባለ ይከናወናል። “አሏህ አክብር አሏህ አክብር” እየተባለ የአላህን ሃያልነት ሙስሊሞች ያስተጋባሉ ይላሉ ሸህ ሙሐመድ፡፡ ይህም በአላህ የታዘዘ በነብዩ ሙሐመድ በተግባር የተፈጸመ ስለመኾኑ ነው የሚያስረዱት፡፡
የዒድ ሶላት ሥነ ሥርዓትን በዓደባባይ መፈጸም፡- ሌላው ሃይማኖታዊ አስተምህሮንና ትእዛዛትን መሰረት አድረጎ የሚፈጸም ተግባር እንደኾነ ነው የሚያስረዱት፡፡ አማኞችም የሶላት ስግደት ወደሚካሄድባቸው ስፍራዎች በመሄድም ይሰግዳሉ፣ ዱዓ (ጸሎት) ያደርጋሉ።
👉ዒዱን በደስታ ማሳለፍ፡- በመጨረሻም የዒድ በዓል የደስታ በዓል በመኾኑ አማኞች የሚደሰቱበትን መልካም ተግባራት ያከናውናሉ። ደስታን መግለጽ፣ ደስታን ማጋራት፣ ለሌሎች ማካፈል አንዱ የአምልኮው ሥርዓት አንድ አካል ነው ይላሉ ሸህ ሙሐመድ።
👉 የተቸገሩትን ማሰብ፡- በዒድ እለት የተቸገሩትን ማገዝ ያዘኑትን ማስደሰት፤እንባቸውን ማበስ፤ወላጅ የሌላቸው መጠጊያ ያጡ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ከዚህ ቀደም ዒድን በደስታ ያሳልፉ የነበሩ ዛሬ በየምክንያቱ ተፈናቅለው በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ማሰብ እና መርዳት ከአምላክ ጋር በበጎ ተግባር ለመቃረብ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ሼህ ሙሐመድ ፡፡
ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ የእርስ በርስ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችሉ፤ ከወዳጅ ዘመድ ከጎረቤትም ጋር አብሮ ማእድ በመጋራት በደስታ ማሳለፍ፤ ደስታን ማጋራት አንዱ የአምልኮው መገለጫ እንደኾነም ነው የሚናገሩት፡፡
ሼህ ሙሐመድ አንዋር እንዲህ ያሉ መልካም እሴቶችና ተግባራት ሁሉ የዒድ አልፈጥር ልዩ መገለጫዎች ናቸውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል ፡፡
ለመላው እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መልካም ዒድ አልፈጥር በዓል እንዲኾንላቸውም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!