“የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል” የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል

109

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የበዓሉ የዒድ ሶላት ተጀምሮ እሰከሚጠናቀቅ የሚዘጉ መንገዶች እንደሚኖሩም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በየዓመቱ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነው የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በመላው የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ነው። በመሆኑም በአዲስ አበባ ስታዲዮም እና በዙሪያው የሚከናወነው የበዓሉ የዒድ ሶላት ላይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት እንደመሆኑ የሶላት ስነ-ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና የበአሉ ድባብ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የዕምነቱ ተከታዮች እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለይም ለዒድ ሶላት የሚመጣውን ህዝበ ሙስሊም በማስተባበር እና የበዓሉን ድባብ ሊያደፈርስ የሚችል ችግር እንዳያጋጥም ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሚያደርጉት ተሳትፎ የጎላ እንደሆነ የጠቀሰው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዘንድሮው በዓልም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከዕምነቱ አባቶች እና ከወጣቶች ጋር ተገቢው ውይይት መደረጉን ገልጿል።

የዕምነቱ ተከታዮች በየአካባቢያቸው በዓሉን ሲያከብሩም ሆነ ወደ ዒድ ሶላቱ ሲመጡ እንደወትሮው ሁሉ የፖሊስን መስተንግዶና ትዕዛዝ በማክበር ተባባሪ እንዲሆኑ እና የበዓሉ ስነ ስርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ መላው የከተማችን ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል። በዚህ የፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ በአካባቢያችሁ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ስትመለከቱ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲልም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ መልዕክቱን ያስተላልፋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 1444ኛው የዒድ አልፈጥር ረመዳን በዓል የዒድ ሶላት ተጀምሮ እሰከሚጠናቀቅ ለተሸከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች እንደሚኖሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች ከዚህ በታች የተገለፁት መንገዶች ዝግ መሆናቸውን ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙም አሳስቧል።

በዚህም መሰረት
– ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ
– ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ
– ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት
– ከፒያሣ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቸርችል ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ
– ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
– ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ
– ከሲኒማ ራስ በጎላ ሚካኤል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎላ ሚካኤል መስቀኛ
– ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ
– ከባሻ ወልዴ ችሎት በኦርማ ጋራዥ ወደ ፍል ውሃ መስኪድ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት
– ከጎፋ በቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ወደ ለገሐር አዲሱ መንገድ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ
– ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ
– ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለቀላል መኪና የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ እንዲሁም ለከባድ መኪና አጎና ሲኒማ አካባቢ
ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከለሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን እያስተላለፈ ለእምነቱ ተከታዮች በሙሉ በዓሉ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መልካም ምኞቱን ይገልፃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article“በዒድ አልፈጥር በዓል የሚከናወኑ ተግባራትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮው”