
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀው የረመዷን ወር ቅዱሱ ወር በመባል ይታወቃል፡፡ ወሩ በጾም የሚያልፍ በመኾኑ ሴቶች ረጅም ሠዓት በሥራ ተጠምደው ያሳልፋሉ፡፡ ጎን ለጎንም ጾም፣ ስግደት ዱዓ ያደርጋሉ፡፡ የሥራ መብዛት ከጾማቸው፣ ከስግደታቸው እና ከዱዓቸው አያግዳቸውም፡፡
የባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪዋ ወይዘሮ ሰይዳ ገበያው ባለትዳር እና የልጆች እናት ናቸው፡፡ ረመዷን ለእሳቸው የሃጢያት ማቅለያ ከአምላክ ጋር መገናኛ ወር ነው፡፡ በረመዷን ወቅት የእናቶች ሥራ ጠንከር ይላል፤ ወይዘሮ ሰይዳ ግን በፍቅር ያልፉታል፡፡ ሥራው የረመዷን ጾም ከመጀመሩ በፊት ለጾሙ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ቀድሞ በመግዛት ይጀመራል፡፡ ይኽም ጾሙን በአግባቡ እንዲጾሙ ያስችላቸዋል፡፡ ቀድመው መሸመታቸው ደግሞ በተደጋጋሚ ወደገበያ እንዳያቀኑ ረድቷቸዋል፡፡
ወይዘሮ ሰይዳ ከመጾም፣ ሶላት ከመስገድ እና ድዋ ከማድረግ ባሻገር ሲጾም የዋለው የቤተሰባቸው አባል የሚያፈጥርበት ሾርባ፣ ኩኪስ፣ ዳቦ እና ሌሎች ምግቦችን ማዘጋጀት የዘወትር ተግባራቸው መኾኑን ነግረውናል፡፡
ከቤተሰቡ በተጨማሪ ለተራቡ እና ለተጠሙ ሰዎች በጎ ሲያደርጉ፣ ሌሎችም እንዲያደርጉ ሲያስተባብሩ የሚደርስባቸው የለም፡፡ ይኽም በአምላካቸው ዘንድ ዋጋ እንደሚያሰጣቸው ይተማመናሉ፡፡
ለ1ሺህ 444 ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ቤታቸውን እያዘጋጁ፣ ለማፍጠሪያ ምግብ እያበሠሉ፣ እንዲሁም ለሥጦታ የሚኾኑ ነገሮችን እያዘጋጁ ነው፡፡
ረመዷን የእዝነት የመተሳሰብ ወር በመኾኑ ወይዘሮ ሰይዳም ያላቸውን እያካፈሉ እንደሚያሳልፉት ተናግረዋል፡፡ የትዳር አጋራቸው የቤት ሥራ ባያግዟቸውም የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በመሥጠት እና በሃሳብ በመደገፍ ረገድ እንከን እንደማይወጣላቸው ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ ሰይዳ ለኹሉም የእምነቱ ተከታይ እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወይዘሮ መሬም ማሩ ሌላዋ የቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ የትዳር አጋራቸውን በሞት በማጣታቸው 3 ልጆቻቸውን በብቸኝነት አሳድገዋል፡፡
ወሩ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ወር ተብሎ ስለሚታወቅ ስግደት፣ ጾምና ድዋ በሰፊው ይደረጋል፤ ወይዘሮ መሬምም ከሥራቸው ጋር አጣጥመው ከፈጣሪያቸው የታዘዘውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ መሬም ልጆቻቸውን ለማሳደግ በርካታ ውጣውረዶችን ቢያሳልፉም ልጆቻቸውን ከሚፈልጉት ደረጃ አድርሰዋል፡፡ ሌሊት ዳቦ ሲጋጋሩ አድረው ቀን ቀን እየሸጡ ይውላሉ፡፡ ጎን ለጎን ቤተሰቦቻቸው የሚያፈጥሩበትን ምግብ ያዘጋጃሉ የአባት እና የእናትን ኀላፊነት ቢሸከሙም ከብዷቸው ግን አያውቁም፡፡ ሴቶች ጠንካራ መኾን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
“የሥራ መብዛት ጾሙን አላስተጓጎለውም እንዲያውም እንድጠነክር አገዘኝ እንጅ” ነው ያሉት፡፡ “አሁን ለኢድ አልፈጥር በዓል እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ቤቴን ሙሉ ማድረግ ይጠበቅብኛል፡፡ የለመዱ ዘመድ ወዳጆቼ እንኳን አደረሰሽ ለማለት ይመጣሉ፡፡ ጎረቤቶቼ ጋር አብሬ ለመዋል ቀድሜ ምግብ ማዘጋጀት፣ ቤት ማጽዳት፣ የሚገዛዙ ነገሮች መግዛት አለብኝ፤ እንዲሁም ደንበኞቼ እንዳይጉላሉ ለገበያ የማቀርበውንም ጎን ለጎን እያዘጋጀሁ ነው” ብለዋል፡፡
ወይዘሮ መሬም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በዓሉን በመሰላም፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት ማክበር ከአባቶቻችን የወረስነው በመኾኑ ለልጆቻችን በማውረስ ማስቀጠል የእኛ ግዴታ ነው፤ ማንኛውም የእምነቱ ተከታይ ያለው ለሌለው በማካፈል በእዝነት፣ በመተሳሰብና በመረዳዳረት ሊያሳልፍ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!