ሁሉም ባለድርሻ አካል ለሠላም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

245

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ1494ኛውን የነብዩ መሐመድ የመውሊድ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን ያስተላፉት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሰኢድ መሐመድ የነብዩ መሐመድ መወለድ ለዓለም ብርሃን “እዝነት”፣ “ረህመት” ነው ብለዋል፡፡ “ነብዩ መሐመድ ስለሰበዓዊና ሴቶች መብት መከበር፣ ዘረኝነት እንዲወገድ፣ ስለአብሮ የመኖር እሴት፣ የተቸገሩ ሰዎችን ስለመርዳት፣ ስለእምነት ነፃነት፣ ስለግልና አካባቢ ንጽሕና መጠበቅ ያስተማሩና ሕግጋትን የደነገጉ የነብዮች ሁሉ መጨረሻ ናቸው” ብለዋል ሼህ ሰኢድ፡፡ ነብዩ መሐመድ ለዓለም ብርሃን መሆናቸውን በመገንዘብና በመደስት ዓለም አቀፉ ሙስሊም ማኅበረሰብ እንደሚያከብረው የገለፁት ሼህ ሰኢድ የነብዩ መሐመድ መወለድ ዋነኛ ዓላማውና ተግባሩ መወለዳቸውን ምክንያት በማደረግ ሙስሊሙ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር፣ ፆታ እና የሀብት መለያዬት ሳይለዬው በጋራ በመሰባሰብ በማብላትና በማጠጣት የነብዩ መሐመድ አስተምህሮዎችን በማውሳት፣ ለትውልድ በማስተላለፍ በፍቅርና በደስታ ማክበር ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በብሔራዊ በዓል ደረጃ እያከበረችው እንደምትገኝ ያስታወሱት ሼህ ሰኢድ የመውሊድ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ለሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም የገፅታ ግንባታ በመሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ የነብዩ መሐመድ መውሊድ በዓል ከሃይኖታዊ እሴቱ በላይ ለሀገርና ለሕዝቦች ሠላም፣ ፈቅር እና የገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ ታላቅና ዕድሜ ጠገብ እንደመሆኑ መጠን በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተደረገው ጥረት ደካማ እንደሆነ በመግለጽ በዓሉን በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ወቅቱ በገሪቱ በርካታ ፈተናዎች የበዙበት ነው›› ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፈተናዎች ከፖለቲካው ባሻገር በሃይማኖት ተቋማት በመግባት በዓማኞችና በቤተ እምነቶች ላይ ከፍተኛ ችግር እያደረሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሰዎች እንደተገደሉና የተለያዩ የእምነት ተቋማት እንደተቃጠሉም አስታውቀዋል፡፡ በቅርብ ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ችግር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ ‹‹የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ግጭቱንም ወደብሔርና እምነት ለማላከክ ሙከራ ተደርጓል፡፡ በየጊዜው እየተፈጠረ ያለው ችግር የሚያሳስብ በመሆኑ የሃይማኖች አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ወጣቶች ለሠላም በሰፊው መሥራት አለባቸው›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ለዘማናት በመከባበር እና በመቻቻል የኖረው ሕዝብ ለግል ጥቅማቸው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መረበሽ እንደማይገባውም አሳስበዋል፡፡ ሠላም እንዲሰፍን ቤተ እመነቶች የቤት ሥራቸው ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ ሃይማኖት የሠላም ችግር ሊሆን እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው የሠላም ችግር የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ የመስጅድ ዑለማዎች በየሶላቱ ኅብረተሰቡን በማስተማር፣ ወጣቶችን በመምከር “ደዋ” በማድረግ የሀገር ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የዕለት ከዕለት ተግባራቸው እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን በተመለከተ አለመግባባት እንደተፈጠረ ያነሱት ሼህ ሰኢድ ላለለፉት 40 ዓመታት ከቀበሌ ጀምሮ እየተመረጠ ሲሰራ የኖረው መጅሊስ በሕጋዊ መንገድ እስኪቀዬር ድረስ ሕጋዊ ሥራውን መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ጉዳዩ ሕጋዊ እንዲሆን በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸው ሌሎች ሕገ ወጥ ምርጫዎች እንዲቆሙም አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት መዋቅርም ጉዳዩን ታሳቢ በማድረግ ሕገ ወጦችን በማስቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ሼህ ሰኢድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ በወቅታዊ ጉዳይ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን በመንከባከብ በዓሉን የጋራ በዓል አድረገው እንዲውሉ በማድረግ መሆን እንደሚገባውም ሼህ ሰኢድ አሳስበዋል፡፡ በዓሉ የሠላም፣ ፍቅርና የደስታ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleየፀጥታ ኃይሉ የበረሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አበረታች የመከላከል ተግባር እየፈፀመ መሆኑ ተገለፀ፡፡
Next articleከ60 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረው ተጨማሪ 28 ሚሊዮን ብር ለማጭበርበር ሂደት ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥ ሥር ዋሉ፡፡