“ቢላል የእስልምና ሃይማኖት እንቁ ፣የኢትዮጵያም ኩራት ነው” ሼህ ሙሐመድ አንዋር ጁኔድ

138
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ቀን ነቢዩ ሙሐመድ በነብይነት የመላካቸውን ዜና የመካ ሕዝብ ሲቀባበለው ከቢላል ጆሮ መድረሱን ተከትሎ እስልምናን በምርጫው እንደተቀበለ በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር ጁኔድ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
ቢላል ኢብን ረባህ ፦
  • ነቢዩ ሙሐመድ “በጀነት ውስጥ ከእኔ ቀድሞ የእግርህን ኮቴ ሰማሁት” ያሉለት ድንቅ ሰው፣
  • ለአዛን አድራጊነት (ሙዓዚንነት) በነቢዩ ሙሐመድም በአንደኝነት የተመረጠ የተወዳጅ ድምጽ ባለቤት፤ ቢላል ኢብን ረባህ!
ቢላል ኢብን ረባህ ማነው?
በእስልምና ሃይማኖት በጽኑ አማኝነት፣ በታማኝነት፣ ላመኑበት ሟችነት፣ በሀቀኝነት፣ በሩህሩህነት ፣ በምርጥ አዛን አድራጊነት ፣በአጠቃላይም ከሃይማኖተኛነቱም ባሻገር በሰዋዊነት ከፍ ብለው በበጎ ከሚነሱ ሰዎች መካከል አንዱ ነው – ቢላል ኢብን ረባህ። የዘር ሐረጉ ከኢትዮጵያ ይመዘዛል።
ቢላል የነቢዩ ሙሐመድን የነቢይነት ታሪክ እና አስተምህሮዎቹን ፣ነቢዩ የተነሳበትን ዓላማ ከሰማበት ከተረዳበት ቅጽበት ጀምሮ ልቦናውን ለእስልምና ሰጠ።
በዚህም በወቅቱ እስልምናን ከማይቀበሉ ይልቁንም አውጋዥ ከነበሩ አካላት የተነሳበት ቁጣና ስቃይ በረታ፤ ግን ቢላልን ከልቦናው ሊያሸፍቱት አልቻሉም።
የመጣውን ሁሉ መከራ ተቀብሎ በአቋሙ ጸንቶ፣ በጽናቱም ፤ በአገልግሎቱም ስሙንና ዝናውን ከፍ አድርጎ ናኘ።
“ስለ ቢላል ተናግሬ አልጠግብም” የሚሉት ሼህ ሙሐመድ አንዋር ጁኔድ፤ ቢላል ከእስልምና ሃይማኖት ውለታው ባሻገር የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት የላቀ አበርክቶ እንዳለው ነው የሚያስረዱት።
በየዓለሙ ዳርቻ ስንንቀሳቀስ ይላሉ ሼህ ሙሐመድ “ከኢትዮጵያ ነው ብዬ ራሴን ሳስተዋውቅ ኦ- ከቢላል ሀገር” የሚሉንን ማሰብ ብቻ በቂ ነው ይላሉ።
ስለቢላል ኢትዮጵያዊነት የሚያውቅ ሁሉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ባሕል፣ ሃይማኖትና ሉዓላዊት ሀገር ይጠይቃል፣ ያጠናል ፣ይረዳል። እናም ቢላል በየዘርፉ ሀገራቸውን ካስጠሩ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ተርታ ይጠቀሳል ።
“ቢላል የእስልምና ሃይማኖት ጠበቃ ፣የኢትዮጵያም ኩራት ነው” ሲሉም ነው የተናገሩት ሼህ ሙሐመድ አንዋር ጁኔድ።
ቢላል ከባርነት ተነስቶ ወደ ላቀ የእስልምና ሃይማኖት የአገልግሎት ጥግ የደረሰ ሃይማኖተኛነቱን የሚያስረዱት ሼህ መሐመድ ፣ቢላል በባርነት ከተሰደዱ ወላጆቹ የተወለደ እሱም ለባርነት የተዳረገ ስለመኾኑ ያነሳሉ።
“ቢላል ከባርነት እስከ ተመራጭ አዛን አድራጊነት”
እስልምናን በወጣትነቱ የተቀበለው፣ በጣም ውብና ልዩ በኾነው ድምጹ የሚታወቀው ቢላል ከእስልምና በፊት በነበረው ሕይወቱ “ባሪያ” ነበር።
የቢላል ወላጆች ወደ መካ የሄዱ ባርያዎች ስለመኾናቸው በታሪክ ተጽፎ ይገኛል። ቢላል የተወለደው ሐማም ከተባለች ኢትዮጵያዊት ፣ አባቱ ደግሞ ረባህ የተባለ ጥቁር አረብ ባርያ እንደነበሩ ነው ታሪኩ የሚያስረዳው።
ቢላል የተወለደው ነብዩ ሙሐመድ ከተወለዱበት ቅዱስ ከተማ መካ ዉስጥ እንደኾነ ነው የሚነገረው።
ከባርያ የተወለደው ቢላል እሱም የበኒ ጁመሃ ጎሳ አባል የነበረው የኡመያ ኢብን ኸለፍ ባሪያ ኾነ።
አንድ ቀን ነቢዩ ሙሐመድ በነብይነት የመላካቸው ዜና የመካ ሕዝብ ሲቀባበለው ከቢላል ጆሮ ደረሰ። እናም ቢላል ነቢዩ ሙሐመድ ስለተነሱበት ዓላማና ስለሚያስተምሩት ትምህርት ግንዛቤ ሊያገኝ ቻለ ይላሉ ሼህ ሙሐመድ።
ሼህ ሙሐመድ እንደሚሉት፤ ቢላል ስለነብዩ ጥልቅ እውቀት ካገኘ በኋላ ፣ የእምነት ምርጫውን ይፋ ማድረግ እንዳለበት እና እንደወሰነም ከታሪኩ መረዳት ይቻላል ነው የሚሉት።
ታዲያ ቢላል ወደ ነቢዩ ሙሐመድ በመሄድ እስልምና ለመቀበል መወሰኑን የሰሙ ሁሉ ተቃውሟቸውን አሳዩ። በተለይም ኡመያ ኢብን ኸለፍ የተባለው የቢላል አሳዳሪ የ”ባሪያ”ውን መስለም እንደ ታላቅ ነውር እና ንቀት ቆጠረው።
ኡመያ እንዲህም አለ፥ “ይህ ኮብላይ ባሪያ በመስለሙ ጸሀይ ተመልሳ የምትጠልቅ አይመስለኝም” ሲል ንቀቱንም ቁጭቱንም ገለጸ።
ማስጠንቀቂያውንም ኾነ ማስፈራሪያውን አልፎ ቢላል እስልምናን ተቀብሏል። ቢላል በሃይማኖቱ በርካታ ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል።
እንደ ሼህ ሙሐመድ ማብራሪያ ፤ በምርጫው የተቀላቀለውን እስልምና አስገድዶ ለማስለቀቅ ቢላልን በእንግልት፣ በግርፋት ቢቀጡትም፣ቢያሰቃዩትም ቢላል ግን ከስጋዊ ሕመም መንፈሳዊ የበላይነትን መርጧልና ለጠላቶቹ የሚረታ አልኾነም።
ይልቁንም እነሱ ሲያሰቃዩት በተደጋጋሚ “አሐድ! አሐድ” አሐድ! … “ በማለት የአምላክን አንድነት ያውጅ ነበር፣ ይሉታል።
የቢላልን በሃይማኖቱ መጽናት፣ የአሳዳሪዎቹም ሃይማኖትህን ቀይር በሚል ያሳደሩበትን የግፍ ጥግ የሰማ አቡበክር ሲዲቅ የተባሉ ሰው መጡ።
ቢላልን ከኡመያ ለመግዛት ተስማሙ፡፡ እኒህ ሰው ቢላልን ለመግዛት የተስማሙት ለራሳቸው ባሪያ ሊያደርጉት ሳይኾን ከስቃዩ ገላግለው ነጻነቱን ሊያውጁለት ነበር ይባላል።
ቢላል ነጻነቱን ካገኘ በኋላ ወደ ነብዩ መሐመድ በመሄድ ሙሉ ጊዜውን ለእስልምና ሰጠ። ቢላል በእምነቱም የበረታ፣ የታመነ፣ ሀቀኛ፣ ታማኝና ብልህ ሰው መኾኑ በብዙወች ዘንድ ታወቀ። ነብዩ መሐመድም ቢላልን ለአዛን አድራጊነት (ሙዓዚንነት) መረጡት። በተጨማሪም የመዲና የግምጃ ቤት ኀላፊ አድርገው ሾሙት።
ከአቡመህጅር፣ ከቢመክቱም ቀድሞ ነብዩ ሙሐመድ ቢላልን ቀዳሚው አዛን አድራጊ አደረጉት። ከሦስቱ አዛን አድራጊዎች ሁለቱ አዛን ሊያድርጉ የሚችሉት ቢላል በቦታው ከሌለ ብቻ እንደኾነም ነው የሚነገረው።
ከዝቅተኛ ማኀበረሰብ ወጥቶ ለታላቅ ሃይማኖታዊ አገልግሎት የበቃ፤ በወቅቱ ለነበረው የጣኦት አምልኮ እንቢ ያለው ቢላል ለትልቅ እስላማዊ አገልግሎት በቃ።
የኣዛን ጥሪ በሚመጣበት ጊዜ በነብዩ ሙሐመድ ከተመረጡ ቀዳሚው አዛን አድራጊ የሶላት ተጠሪ ቢላል ኾነ፡፡
ትልልቅ የጎሳ መሪዎች ነን የሚሉት አረቦች ባሉበት፣ የቁሬሽ ነገሥታቶች ባሉበት፣ እኛ የነገድ ፊት አውራሪዎች ነን የሚሉ በዘር በሚመጻደቁበት ፊት መስጊድ ጣራ ላይ ቁሞ “አሏህ አክብር አሏህ አክብር” በማለት አዛኑን ጀመረ፣ ይሉናል ሼህ ሙሐመድ፡፡
ቢላል ትልቅ እውቀት የተቸረው፣ ለራሱ ክብር የሚሰጥና በራሱ የሚተማመን ሰው እንደኾነ ምስክር ሰጭዎቹ ይናገራሉ።
የኋላ ኋላ ቢላል ዝናው እየናኘ ሲመጣ፣ ጓደኞቹ ሲያሞግሱት በትህትና አንገቱን ደፋ እያደረገ “ትናንት ባሪያ የነበርኩ ሐበሻ ነኝ” ይላል አሉ። እነሱ ግን “የእኛ ልዑል” ብለው ያሞካሹት እንደነበር በታሪክ ተቀምጧል ።
ሼህ ሙሐመድ፤ የቢላልን አበርክቶ ሲያስረዱ ቢላል ተምሳሌትነትን ለጡቁር ሕዝቦች ሁሉ አስተምሯል። ቢላል ለትውልድ ሁሉ እምነቱን ለሚጋሩት እና ለማይጋሩትም ወገኖች ያስተማረው ትምህርት የሕሊና ነጻነትን አሰቃቂ ቅጣት ሊበግረው እንደማይችል ነው።
ስሙ በአዛን አድራጊነቱ፣ ቀልብ በሚሰርቀው ድምጹ የሚታወቀው ቢላል ኢብን ረባህ፤ አል ሐበሽይ፣ ቢላል ኢብን ሪያህ በሚሉ ቅጽል ስሞቹም ይጠራል። ነቢዩ ሙሐመድ ቢላልን እጅግ እንደሚወዱት፤ እንደሚኮሩበትም ነው የሚነገረው። እንዲያውም አንድ ጊዜ ቢላልን እንዲህ ሲሉ ጠየቁት አሉ ” ቢላል፣በጀነት ውስጥ ከእኔ ቀድሞ የእግርህን ኮቴ ሰማሁት፣ ምን አድርገህ ነው?” ቢላልም ለነቢዩ በሰጠው ምላሽ “ቅድሚያ በጽዳት እራሴን ንጹህ አደርጋለሁ፣ ቀጥየም እጸልያለሁ፣ ዱዓም አደርጋለሁ” አላቸው ይባላል።
በነብዩ ሙሐመድ ለኣዛን አድራጊነት የተመረጠው ተወዳጁ ቢላል ነብዩ ከአረፉ በኋላ ግን አዛን አላደርግም እንዳለ ሼህ ሙሐመድ ያስረዳሉ። ሼህ ሙሐመድ እንደሚሉት ነብዩን ያስታውሰኛል በሚል አዛን አላደርግም ያለው ቢላል ከስንት ጊዜ በኋላ፣ በስንት ተማጽኖ አዛን እንዲያደርግ ተደርጎ ፣ የጀመረውን አዛን መጨረስ ግን አልቻለም ይሉታል ።
ቢላል በ63 ዓመቱ እንደሞተ ይነገራል። የሞተውም በሻም ሶርያ ውስጥ እንደኾነ፣ በደማስቆ ከተማ እንደተቀበረ ነው መረጃዎች የሚሳዩት። ደማስቆ ውስጥ መቃብሩ አሁን ድረስ እንደሚጎበኝ ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተፈራረመ፡፡
Next articleቢዝነስ ዜና : ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ)