
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ክልል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የጽሕፈት ቤት ኀላፊው አቶ ኃይለሚካኤል ካሳሁን እንደገለጹት የአማራ ክልል ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረገው ያለው አስተዋጽኦ ይበል የሚያሠኝ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡
አቶ ኃይለሚካኤል እንዳሉት ድጋፉ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ድጋፉ ከልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዥ፣ በልገሳ፣ በልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች እና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የተደረገ ታሪካዊ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ ፡-
- ከመንግሥት ሠራተኞች 510 ሚሊዮን 429 ሺህ 476 ብር
- ከባለሃብቱና ከንግዱ ማኅበረሰብ 100 ሚሊዮን 270 ሺህ 876 ብር
- ከአርሶ አደሮች 236 ሚሊዮን 20 ሺህ 455 ብር
- ከድርጅቶችና ተቋማት እንዲሁም ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብር 330 ሚሊዮን 732 ሺህ 723 ብር
- በልገሳ ከተለያዩ የኅብረተስብ ክፍሎች የተሰበሰበ 9 ሚሊዮን 289 ሺህ 665 ብር
- ከልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ብር 31 ሚሊዮን 388 ሺህ 850 ብር ሲሆን
➨ በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን 218 ሚሊዮን 132 ሺህ 46 ብር መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ከማዋጣት በተጨማሪ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ለማድረግ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ባደረገው ያላሰለሰ ተሳትፎ ከ33 ቢሊዮን 797 ሚሊዮን 786 ሺህ 822 ብር የሚገመት የጉልበት ድጋፍ ማደረጉንም አቶ ኃይለሚካኤል አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!