“ዘካ ሃብታሙ ለድሃው፣ ድሃውም ለሀብታሙ እንዲያዝን ያደርጋል” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም

83
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዘካ የሚለው ቃል ትርጉሙ ማጽዳት፣ ማጠብ ወይም ማንጻት ማለት ነው። አማኙ ባለማወቅ ወይም በስህተት ከፈጸማቸው መልካም ያልኾኑ ድርጊቶች ለመጽዳት ወይም ነጻ ለመኾን የሚፈጸም ሰደቃ ወይም ምጽዋት ነው።
አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን ውስጥ ዘካ ብሎ የጠራው የሰጪዎችን ነፍስ እና ገንዘብ ስለምታጠራ ነው፡፡ ነብሳቸውን ከምቀኝነት፣ከስስት፣ከንፉግነት እና ገንዘባቸውን ታጠራለች፡፡
በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋ እና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም እንዳስረዱን ዘካ ለሰዎች በጎ መዋል ነው። ለገንዘብም ንጽህና ነው። ዘካ ያዋድዳል፣ግንኙነትን ያጠናክራል፣ ደካማው እንዲገነባ እና እኩልነት እንዲሰፍን ያደርጋል። መቀራረብና መተሳሰብን ይፈጥራል። ሀብታሙ ለድሃው፣ ድሃውም ለሃብታሙ እንዲያዝን ያደርጋል ብለዋል።
ሼህ ሙሐመድ የተለያዩ የዘካ ዓይነቶች እንዳሉ ነግረውናል። ከነዚህ መካከል ዘካተል ማል አንዱ ነው። ይህ የዘካ አይነት የእምነቱ ተከታዮች ካካበቱት ገንዘብ ከፍለው ለአቅመ ደካሞች የሚያበረክቱት ነው። ዘካተል ማል መስፈርቱን አሟልተው በሚገኙ ባለጸጋዎች ላይ ብቻ የሚጣል ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው።
ይህ የዘካ ዓይነት የሚዋጣው ከንግድ ትርፍ፣ ከሰብል ወይም ከቁም እንስሳት ላይ ሊኾን ይችላል። ባለጸጋዎች የራሳቸው ከኾነው ሀብታቸው 2 ነጥብ 5 በመቶውን ለዘካተል ማል በማዋል ለተቸገሩ ሰዎች አለኝታ እንዲኾኑ ሃይማኖቱ ያዛል ብለውናል።
እንደ ሸህ ሙሐመድ ገለጻ አንድ ባለጸጋ ሰው ራሱ ከሚመገበው ውስጥ 2 ነጥብ 5 በመቶ የሚኾነውን ለተቸገሩት ማበርከት አለበት። የሰደቃው አከፋፈልም ከእያንዳንዱ የቤተሰብ አባላት ላይ የሚታሰብ ይኾናል።
ይህ ማለት ለምሳሌ አስር የቤተሰብ አባላት ያሉት ሰው ለበዓል ዝግጅት 100 ኪሎ ግራም ጤፍ ቢያዘጋጅ ከእያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል 2 ነጥብ 5 በመቶ ተሰልቶ 25 ኪሎ ግራሙን ለተቸገሩት ያበረክታል ማለት ነው።
ሌላው የዘካ ዓይነት ደግሞ ዘካተል ፊጥር ነው። ዘካተል ፊጥር በበዓላት ወቅት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ያላቸውን በማዋጣት ለሌሎች የሚያካፍሉበት የምጽዋት አይነት ነው። በበዓላት ጊዜ ሁሉም ሰዎች ያለምንም ልዩነት በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉም ያግዛል።
ኡለማዎች እንደሚያዝዙት የበዓል ወቅት የዘካ አሰባሰብ ከበዓሉ ቀን አስቀድሞ መኾን አለበት። የኢድ ሶላት ከመሰገዱ በፊት ዘካው ተሰብስቦ መጠናቀቅ አለበት። ይህ የሚኾነው ቀድሞ ተሰባስቦ እና ተዘጋጅቶ ሁሉም የተቸገሩ ሰዎች የደስታ በዓል ማሳለፍ ስላለባቸው ነው።
ሼህ ሙሐመድ እንዳሉት ዘካ በውል ለተለዩ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ነው። ዘካ ምንም ለሌለው እና ልመና ለወጣ ድሃ ይሠጣል። ዘካ ለምስኪኖችም ይሰጣል። ምስኪን ማለት ደግሞ ወጥቶ ለመለመን ያልቻለ፣ ግን ደግሞ በተለያየ ምክንያት የተቸገረ ሰው ማለት ነው።
ሼህ ሙሐመድ ኢድ አልፈጥር በዓልን እንደወትሮው በመጠያየቅ እና በመተዛዘን ማክበር ይገባል ብለዋል። በተለይም በዚህ ወቅት በርካታ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እየተቸገሩ ስለኾነ እነሱን በማሰብ እና በመተጋገዝ አንድነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢድ ሙባረክ! ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺነብዩ የመረጧት፣ አትንኳትም ያሏት”
Next articleየአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡