ʺነብዩ የመረጧት፣ አትንኳትም ያሏት”

124
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአሻገር ተመልክተው በልባቸው አኖሯት፣ ፍትሕ እንዳለባት አዩዋት፣ ሱሃባዎቻቸው ያርፉባት ዘንድ ወደዷት፣ ከሌሎች ሀገራት ለይተው ማረፊያ ትሆን ዘንድ መረጧት፣ መረቋት፣ ሱሃባዎቻቸውም የብሱን አቋርጠው፣ ባሕሩን ሰንጥቀው ገሰገሱባት፣ ነብያቸው እንዳሏቸው አረፉባት፣ ባማረው ቤተ መንግሥት ተስተናገዱባት፣ በፍቅር ተጠለሉባት፣ በደስታ ኖሩባት፡፡
የደከሙ ይበረቱባታል፣ የተከዙ ይጽናኑባታል፣ ተስፋ ያጡ ተስፋ ያደርጉባታል፣ ነጻነት የራቃቸው የነጻነትን ጀምበር ያዩባታል፣ መሻገሪያ የሌላቸው ይሸጋገሩባታል፣ ድል የራቃቸው ድል ያገኙባታል፣ ታሪክ ለተጠሙ ታሪክ ታስተምራለች፣ ስልጣኔ ለጨለመባቸው ስልጣኔን ታሳያለች፣ ቀመር ለሌላቸው ቀመር ቀምራ፣ ምስጢር መርምራ ታመላክታለች ኢትዮጵያ፡፡
ቅዱሳን መጻሕፍት ስሟን ደጋግመው ይጠሯታል፣ አምላክ ይወዳታል፣ ጸጋና በረከትን አድሏታል፣ የተወደደውን፣ የተመረጠውን ሰጥቷታል፡፡ ከተወደዱት የበለጠ ትወደዳለች፣ ከተከበሩት የበለጠ ትከበራለች፣ ከቀደሙት የበለጠ ትቀድማለች፣ ታሪክ ከፍ አድርጎ ከመዘገባቸው የበለጠ ከፍ ብላ ተመዝግባለች፣ የተጻፈችበት ብርና አያረጅም፣ ቀለሙም አይጠፋም፣ እንደ ደመቀ ይኖራል፣ እንደ ከበረ ይዘልቃል እንጂ፡፡
ደጋጎች ይመላለሱባታል፣ ፈጣሪ ምድርን ይጠብቃት ዘንድ ይማጸኑባታል፣ ፍቅርና አንድነት፣ ሰላምና ደስታ ይኖር ዘንድ ይለምኑባታል፡፡ እርሷ በአሻገር ያሉት የሚናፍቋት፣ ክብሯ የገባቸው ስለ ክብሯ የሚናገሩላት፣ ፍቅሯ ያሸነፋቸው በፍቅሯ ውኃ ጥም የሚኖሩላት፣ በምድሯ ይመላለሱ ዘንድ የሚመኟት፣ በምድሯም በተመላለሱ ጊዜ አብዝተው የሚወዷት፣ በራቋትም ጊዜ በትዝታዋ የሚታመሙላት ድንቅ ምድር ናት ኢትዮጵያ፡፡
ዥረቶች እንደፈለጉ ሲፈስሱ በማይታይበት፣ ለዓይን ግቡ የሆነ ጥቅጥቅ ደን በሌለበት፣ በረሃና ሐሩር በበዛበት ምድር አያሌ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በዚያ ምድር ኃያላን ነገሥታት ተነስተዋል፣ በየዘመናቸው አያሌ ጀብዱዎችን እየሠሩ ለተከታዮቻቸው እያስረከቡ አልፈዋል፡፡ በዚያ ምድር ነገሥታት፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ የጦር አበጋዞች እና ጦረኞች በግርማ ታይተዋል፡፡ ጠቢባን እና መምህራንም ተነስተዋል በበረሃማው የዓለም ክፍል በመካከለኛው ምሥራቅ፡፡
በዚሕ በመካከለኛው ምሥራቅ በመካና በመዲና ከተነሱ ነገሥታት፣ መኳንንት፣ መሣፍንት፣ የጦር አበጋዞች፣ ጦረኞች እና ነብያት ሁሉ የላቁ አንድ ሰው በአላህ ፈቃድ ተነሱ፡፡ ዘመኑም 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ ነበር፡፡ እኒህም ሰው ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ዘንድ ከእርሳቸው ጋር የሚተካከል ከእርሳቸው አስቀድሞም፣ ከእርሳቸው ተከትሎም የመጣ ነብይ የለም፡፡ እርሳቸው በአላህ የተመረጡ፣ በጅብሪል የተጠበቁ፣ የአላህ መልእክተኛ እና ተገዢ የሆኑ የመጨረሻው ነብይ ናቸው፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንደሚሉት ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስቀድሞ ቁጥራቸው የበዛ ነብያት እና ሩሱሎች ተነስተዋል፡፡ በመጨረሻ የመጡት ግን ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ እርሳቸው ለአረቡም፣ አረብ ላለሆነውም፣ ለመላው ዓለም፣ ለሁሉም ሰው የተላኩ የመጨረሻ ነብይ ናቸው፡፡ ላኪያቸውም አላህ ነው፡፡ አላህ እሳቸውን ሲልካቸው ያለፈውን ታሪክ የሚገነዘቡ፣ መጪውን ዓለም እና የወዲያኛውን ዓለም እንዲያውቁ አደረጋቸው፡፡ ጀብሪል ጠበቃቸው፣ ከሰማይ እየወረደ በጎናቸው ቆመላቸው፣ ያስተምራቸዋልም፡፡
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከመወለዳቸው በፊት ለታላቅነታቸው ምስክር የሆኑ ታምራት ይታዩ ነበር ይሏቸዋል ፕሮፌሰሩ፡፡ ጊዜው ደረሰ፡፡ ለታላቅ ነገር የታጩት፣ የአላህ መልእክተኛ ተወለዱ፡፡ ነብዩ አባታቸውን በሁለት ወራቸው፣ እናታቸውን ደግሞ በሥድስት ዓመታቸው አጡ፡፡ ወላጆቻቸውን ባጡም ጊዜ በረካ ሃላሐበሺያ (ሐበሻዊቷ እመቤት) የተሰኘች የሐበሻ ሴት እሳቸውን ያሳድጉ ዘንድ ተመረጡ፡፡ የነብዩ እናት ይህ ልጅ ታምረኛ ልጅ ነውና አደራ ብለው የአደራ መልእክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ሐበሻዊቷ እመቤት እንዴት ወደዚያ ሄደች ለሚለው የአላህ ጥበብ አለበት ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ይህችም ሴት ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ኖሩ፡፡ ከእናታቸው የተቀበሉትን አደራም ፈፀሙ፡፡
እኒህ አላህ የመረጣቸው ነብይ አርባ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ታማኙ መሐመድ፣ ሐቀኛው መሐመድ፣ ፍትሐዊ መሐመድ እየተባሉ ይጠራሉ፣ ነጋዴዎች አደራ የሚያስቀምጡ ከእሳቸው ነበር ነው ያሉኝ፡፡
በ570 የተወለዱት ነብዩ በ610 አዲስ አዋጅ መጣላቸው፡፡ የመጀመሪያው የቁራን ምዕራፍ ወረደላቸው፡፡ የወረደላቸውን ቁራን በዋሻ ውስጥ ሆነው አነበቡ፡፡
ከዚህም በኋላ የአላህ መልእክተኛ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩበትን ለዓለም ሁሉ ያውጁና ይነግሩ ዘንድ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ታዘዙ፡፡ እሳቸውም የታዘዙትን አደረጉ፡፡ ኑ ወደ አንድ አላህ አሉ፡፡ ይህን ባሉ ጊዜ ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡ ለምን ከተባለ በመካ ጣዖቶችን የሚያመልኩ ነበሩና ይላሉ ፕሮፌሰር አደም፡፡ በዚያ ምድር ከወርቅ የተሠሩ፣ ከብርም የተሠሩ፣ ከነሀስም የተሠሩ፣ ከእንጨትም የተሠሩ ጣዖቶች ነበሩ፡፡ የእርሳቸው አዋጅ እነዚህን ጣዖቶች የሚያስተው፣ አላህን ብቻ እንዲያምኑና እንዲያመልኩ የሚያደርግ ነውና ተቃውሞው በረታባቸው፡፡
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተነሱበት ዘመን አራት ኃያላን መንግሥታት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አራት ኃያላን መንግሥታት መካከል ኢትዮጵያ ወይም የሐበሻ መንግሥት አንደኛው ነበር፡፡ በዚህም ዘመን ንጉሥ ነጋሲ ( ነጃሺ፣ አልነጃሽ) ነግሠው ነበር፡፡ የእኒህ ንጉሥ በዚያ ዘመን መንገሥ የአላህ ፈቃድና ጥበብ አለበት ነው ያሉኝ ፕሮፌሰሩ፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመካ ተቃውሞው ሲበረክትባቸው፣ ፈተናውም ሲበዛባቸው ተከታዮቻቸውን ይልኩ ዘንድ ፍትሕ ያለባት ሀገር ፈለጉ፡፡ በዚያ ዘመን የእርሳቸውን እመነት መከተል ያሳስራል፣ ያስገርፋል፣ ያሳድዳል፣ ያስገድላልና፡፡ ሀገር በፈለጉም ጊዜ ኢትዮጵያ የተሰኘች፣ ደጋግ ነገሥታት የሚነግሡባት፣ ፍትሕና ስርዓት የሚጸናባት፣ ሐቅ ያለባት ሀገር አለችና እርሷን መረጧት፡፡
ኢትዮጵያን ያስመረጣቸው ማንም አይደለም ፈጣሪያቸው አላህ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር አደም፡፡ እናንተ ተከታዮቼ ሆይ ሐቀኛ ንጉሥ ወደ አለባት የእውነት ምድር ሂዱ አሏቸው፡፡ እውነትና ሐቅ ከተገኘማ ብለው የነብያቸውን ትዕዛዝ ሰምተው 12 ወንዶች 4 ሴቶች ከሸሂባ ወደ አዶሊስ አቀኑ ነው ያሉኝ፡፡ አዶሊስ በዚያ ዘመን መናገሻውን አክሱም ላደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የንግድ ትሥሥር የሚደረግባት ወደብ ነበረች፡፡ የነብዩ መሐመድ መልእክተኞች ከአዶሊስ ንጉሡ ወደ ሚገኙበት ቤተ መንግሥት አቀኑ፡፡ እውነትም ነብዩ እንዳሉት እውነተኛ ንጉሥ እና ሐቀኛ ምድር አገኙ፡፡ እውነተኛ ንጉሥ በሐቀኛ ምድር ነግሠዋልና፡፡ እነዚያ ሱሃባዎችም የተመረጡ ነበሩ፡፡
እኒህ ብቻ አይደሉም፤ ሌሎችም እውነት ወደ አለባት ምድር ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ የመጡትንም ንጉሡ በክብርና በፍቅር ተቀበሏቸው፡፡ ኢትዮጵያና እስልምናም የተሳሰሩት በዚያ ዘመን ነበር ነው ያሉኝ ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡
ኢትዮጵያ የእውነት ምድር በመባል አንደኛ ናት ይሏታል ፕሮፌሰሩ፡፡
ከመዲና አስቀድሞ ከመካ ቀጥሎ እስልምናን ተቀብላለችም ይላሉ፡፡ ነጋሲ ወይም ነጃሺ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ ታላቅ ንጉሥ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም በዚህ እንኮራለን ነው ያሉኝ፡፡
ዛሬ ላይ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች የኢትዮጵያ ባለ እዳ ናቸውም ይሏቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅዱስ ቁራን፣ በነብዩ ሐዲስ ውስጥ የተገለፀች ክብር ያላት ሀገር ናት ነው ያሉኝ፡፡ ነብዩ ያከበሯት ሀገርና ሕዝቦች በመሆናችን ኢትዮጵያውያን በሌሎች ሀገራት ስንሄድ እንከበራለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ነብዩ አደራ እንዳትነኳት ያሏት የተወደደች እና የተከበረች ሀገር መሆኗንም አስገንዝበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በነብዩ ከበሬታና ወዴታ ምክንያት በሙስሊሞች ዘንድ የምትወደድ፣ የምትከበር ሀገር ናት፡፡ ይህም መከበርና መወደዷ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ነው የነገሩኝ፡፡
የነብዩ ሱሃባዎች አጽም ያረፈበትን የአልነጃሽ መሰጂድን እና ሌሎችን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማድረግ እና የኢትዮጵያን ታሪክ ለዓለም በመንገር ኢትዮጵያን በዓለም ፊት ከፍ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ይህችን ታላቅና የተከበረች ሀገር ማክበርና መጠበቅ የልጆቿ ግዴታ መሆኑንም ነግረውኛል፡፡ ኢትዮጵያን እየጣሉ ወደ ውጭ ከመማተር ይልቅ በተወደደች ሀገር የተወደደ ሥራ ሠርቶ ኢትዮጵያን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውድቀትን እና ልባዊ መራራቅን እንጅ ክብር እና ከፍታን አያገኝምና በዓሉን ስናከብር በአንድነት በፍቅር ይሁን” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት
Next article“ዘካ ሃብታሙ ለድሃው፣ ድሃውም ለሀብታሙ እንዲያዝን ያደርጋል” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም