
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ 600 ሺህ የሚደርስ የግሪሳ ወፍ ተከስቷል፡፡ የግሪሳ ወፉ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው ‹ያለን› እና ‹ተሬ› ተብለው በሚጠሩ ሁለት ቀበሌዎች መሆኑን የቀወት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡ የግሪሳ ወፉ በአካባቢው ከጥቅምት 23 ጀምሮ እንደተከሰተም ነው የቀወት ወረዳ ግብርና ምፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ማምሻ የተናገሩት፡፡
የወፍ መንጋው አስካሁን በሰብል ላይ ያስከተለው ጉዳት በውል ባይታወቅም ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች በወንጭፍና በሌሎች ባሕላዊ የወፍ ማባረሪያ ዘዴዎች እየተከላከሉ ነውም ተብሏል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው የወፍ መንጋውን በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ታግዞ ማስወገድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል መንግሥታት አካላት ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ እስከዚያው ግን የግብርና ባለሙያዎች ለአካባቢው ማኅበረሰብ ግንዛቤ በመፍጠር በባሕላዊ መንገድ እየተከላከሉ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ በበኩላቸው አውሮፕላን ተጠቅሞ የወፍ መንጋውን ለመከላከል ጥረት እተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት በአውሮፕላን በታገዘ የኬሚካል ርጭት የወፍ መንጋውን ማስወገድ ያልተቻለውም አውሮፕላኖቹ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የበረሃ አንበጣ ምክንያት በሥራ በመጠመዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ የአውሮፕላን ድጋፍ ከሚመለከታቸው አካላት ሲጠይቅ እንደቆየና አንድ አውሮፕላን ማግኘቱንም ጠቁመዋል፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት በአውሮፕላን የታገዘ የርጭት ሥራ እንደሚጀመርም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የኬሚካል መርጫ አውሮፕላቹ በተደጋጋሚ ብልሽትና በመልክአ ምድር አለመመቸት ምክንያት በአማራ ክልል ሦስት ዞኖች ያጋጠመውን የበረሃ አንበጣ መንጋም ለመከላከል ፈተና ሆኖባቸው እንደቆዬ መዘገባችን ይወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ፎቶ፡-ሽፈራሁ ተሾመ