“የተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውድቀትን እና ልባዊ መራራቅን እንጅ ክብር እና ከፍታን አያገኝምና በዓሉን ስናከብር በአንድነት በፍቅር ይሁን” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

75
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1444ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የእስልምና ጉዳዩ ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሸህ አብዱረህማን ሱልጣን ሁሉም የክልሉ ሙስሊሞች በዓሉን ሲያከብሩ በአንድነትና በመቻቻል፣ በፍቅርና በመተባበር ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሸህ አብዱረህማን “የተበታተነ እና የተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውድቀትን፣ ትንሽነትን፣ ልባዊ መራራቅና መናቅን እንጂ ክብር፣ ከፍታና ድልን አያገኝም” ሲሉ በመግለጫቸው አንስተዋል። በመኾኑም መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ሃይማኖቱ በሚያዝዘው መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መኾን አለበት ብለዋል።
በተለይም በተለያዩ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘካ፣ በዘካተል ፊጥርና በመሰል የምጽዋት ዓይነቶች ማስታወስ ይገባል ሲሉም ሸህ አብዱረህማን ገልጸዋል።
ሰላም ወዳዱ ሙስሊም ማኅበረሰብ ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖች ጋር በተለመደው የመተሳሰብ እና የመከባበር እሴት በዓሉን ማክበር እንዳለበትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሸህ አብዱረህማን የሌሎች እምነት ተከታይ ወጣቶች በተለመደው ኢትዮጵያዊ አንድነት እና መተሳሰብ ከሙስሊም ወንድሞች ጋር በመቆም እና ሰላምን በማስጠበቅ በዓሉ በተረጋጋ መልኩ እንዲከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
1444ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥትና የጸጥታ አካላት የተለመደ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም የእስልምና ጉዳዩ ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ገልጸዋል።
ሸህ አብዱረህማን “መጅሊሱ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነና የአላህ እዝነት የሚወርድበት እንዲኾን ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል” ሲሉም መልካም ምኞታቸውን በመግለጫው አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጥጥ ምርት ገበያ ማጣት
Next articleʺነብዩ የመረጧት፣ አትንኳትም ያሏት”