
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከደንበጫ- ፈረስ ቤት -ቢቡኝ- አዴት እየተገነባ ያለው ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ሥራውን የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት እየሰራ ሲኾን ኮር አማካሪ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የማማከር ሥራውን ይሰራል። የሱር ኮንሰልቲንግ አማካሪ ድርጅት ይቆጣጠረዋል። የገንዘብ ምንጩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲኾን የቡሬ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት በበላይነት ይመራዋል። መንገዱ በሁለት አቅጣጫ ይሠራል። ከደንበጫ ፈረስ ቤት 69 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲኾን 1 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ለግንባታ ተመድቦለታል። መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ተይዞለታል።
የመንገዱ መገንባት የወረዳዋ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መኾኑን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪው አቶ ትዕዛዙ ስንሻው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል። የወረዳው ነዋሪዎች በአፄ ኀይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምረው መሠረተ ልማት እንዲሟላላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን አውስተዋል። መሠረተ ልማት ባለመኖሩ በርካታ ነጋዴዎች አካባቢውን እየለቀቁ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተሰደዋል።አሁን እየተገነባ ያለው የአስፋልት መንገድ ወረዳዋን ከሌሎች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ በመኾኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።
መንገዱ ምርት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማድረስ እና ከሌሎች አካባቢዎች ለማምጣት ይረዳል። ለወረዳዋ የሚያስፈልገው ሸቀጣሸቀጥ በሚፈለገው ልክ ይገባል ነው ያሉት። የመንገድ ግንባታው በተጀመረበት ልክ ባለመሠራቱ ቅሬታ ቢኖርም አሁን በተደረገ የአመራር ለውጥ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ለመንገዱ እያደረገ ያለው ድጋፍ እና አመለካከት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። መንግሥት ለሚመለከታቸው አካላት የካሳ ክፍያውን እንዲያጠናቅቅ እና ከሦስተኛ ወገን ነጻ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ሌላው የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪው አቶ ባለው ወርቅነህ በዚህ ዓመት በቂ ማሽን ገብቶ እየሠራ በመኾኑ ደስተኛ ናቸው። ካሁን በፊት አገልግሎት ይሠጥ የነበረው መንገድ ክረምት በጎርፍ ሥለሚበላ ነፍሰጡር እናቶች ሆስፒታል ሳይደርሱ ሕይወታቸው ያልፍ ነበር። ማኅበረሰቡ ይህ ችግር እንዲቀረፍለት ኮሚቴ አዋቅሮ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል። በክረምት ግማሹን መንገድ በእግር ይጓዙና ሲደክማቸው ወይም ሲመሽ መንገድ ለማደር ይገደዱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው መኾኑን ተናግረዋል።መንገዱ ለወረዳው ብቸኛ እና የመጀመሪያ መኾኑንም አንስተዋል። መንገዱ መገንባት በመጀመሩ ባንኮች እና ባለሃብቶች ወደከተማዋ እየገቡ ነው፣ ይኽም የመንገዱ ሲሳይ ነው፤ አሁን በሚሠራበት ወኔ መቀጠል አለበት ብለዋል። ድጋፋቸው እና አብሮነታቸው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በሱር ኮንሰልቲንግ አማካሪ ድርጅት ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጅነር ፀጋዬ ትዕዛዙ የመንገድ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንጻር ጥሩ አፈጻጸም አለው ብለዋል።
አካባቢው ደጋ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ የዝናብ ጊዜ መኖር፣ እና የተቋራጩ አቅም ደካማ መኾን የመንገዱን ግንባታ እንዳጓተተው አንስተዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅን መኾን እና ለልማት የሠጠው አመለካከት ከ57 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገዱ ክፍል ከ3ኛ ወገን ነፃ መደረጉንም ገልጸዋል። አሁን ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሟል ተቋራጩም ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ በግንባታው ላይ ጊዜውን እያሳለፈ ነው። በርካታ ማሽኖች ገብተዋል ነው ያሉት። ለሥራው 21 ዶዘሮች፣ 15 ኤክስካቫተር 11 ሲኖትራክ እና ሌሎችም ማሽኖች ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። በዚህ ዓመት 20 ኪሎ ሜትር ለመገንባትም ታቅዷል ብለዋል።
የቡሬ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሁሉ አለምነህ በበኩላቸው መንገዱ ከተያዘለት ጊዜ አንጻር ዘግይቷል ብለዋል። ኢንጅነሩ ግንባታው ጥቅምት 2016 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም አፈጻጸሙ ገና 15 በመቶ ላይ ብቻ እንደኾነ ነው ያስረዱት። ለሥራው መጓተት የተቋራጩ የአቅም ውስንነት በመኾኑ አሁን በተደረገ የአመራር ለውጥ ጥሩ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢንጅነር ሁሉ የቅርብ ክትትል መደረጉ መፍትሔ እያመጣ ነው፣ ቀጣይ ይሕን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!