ሪያል ማድሪድ እና ሚላን ለግማሽ ፍጻሜ ደረሱ፡፡

173

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ትናንት ምሽት የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ሲደረጉ ሪያል ማድሪድ እና ሚላን ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል፡፡
የመድረኩ ንጉሥ ሪያል ማድሪድ በስታፎርድ ብሪጅ ቸልሲን 2 ለ 0 በኾነ ውጤት በማሸነፍ ነው ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለው፡፡ በሩብ ፍጻሜው የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳው 2 ለ 0 አሸንፎ ወደ ለንደን ያቀናው ማድሪድ ከሜዳው ውጭም ድል ቀንቶታል፡፡ ማድሪድ 4 ለ 0 በሆነ የድምር ውጤት ነው ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለው፡፡ የማድሪድን የማሸነፊያ ግቦች ብራዚላዊው ሮድሪጎ አስቆጥሯል፡፡
በሌላ ጨዋታ ኤሲ ሚላን ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡ በስታዲዮ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና (ሳን ፓኦሎ) ከናፖሊ ጋር የተጫወተው ሚላን በድምሩ 2 ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰው፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳው 1 ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ኔፕልስ ያቀናው ሚላን ጨዋታውን 1 ለ1 አጠናቅቋል፡፡ የሚላንን ግብ ኦሊቨር ጅሩድ ሲያስቆጥር የናፖሊን ግብ ደግሞ ቪክቶር ኦሲሜን አስቆጥሯል፡፡ ሚላን በድምር ውጤት 2 ለ1 ድል በማድረግ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬም ይደረጋሉ፡፡ ባየርን ሙኒክ ከማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በሜዳው ኢትሃድ 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈው ሲቲ የማለፍ ሰፊ እድል ይዞ ወደ ጀርመን ተጉዟል፡፡ የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ የቻምፒዮንስ ሊግ ልምዱን ተጠቅሞ በሜዳው አልያንዝ አሬና ድል አድርጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ይቀላቀል ይሆን? ወይስ ለማንችስተር ሲቲ እጅ ሰጥቶ ሩብ ፍጻሜው ላይ ይቀራል? የሚለው ትኩረትን ስቧል፡፡
አስፈሪ የደጋፊ ድባብ ባለው በአልያንዝ አሬና የሚደረገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡ ያልተጠበቁ ውጤቶችን የሚያሳየው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ዛሬ ምሽትም ያልተጠበቀ ውጤት ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ሰፊ እድል ይዞ ከእንግሊዝ ማንችስተር፤ ከጀርመን ሙኒክ የደረሰው ሲቲ እድሉን አሳልፎ እንደማይሰጥ ይጠበቃል፡፡
የማንችስተር ሲቲው አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ተመልሰው በተቃራኒ ይገጥማሉ፡፡
ፔፕ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲን ቶማስ ቱሄል ደግሞ ቸልሲን እየመሩ በአውሮፓ ቻምፕዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ተገናኝተው ነበር፡፡ በፍጻሜው ጨዋታም ቱሄል ጋርዲዮላን በማሸነፍ ባለ ድል ሆነዋል፡፡ የዛሬው ጨዋታስ ማንን ባለ ድል ያደርግ ይሆን የሚለው የአልያንዙ ጨዋታ መልስ ይሰጣል፡፡
በሌላ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ከቤኔፊካ ጋር ይጫወታሉ፡፡ በመጀመሪያው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ወደ ፖርቹጋል ተጉዞ 2 ለ 0 አሸንፎ የተመለሰው ኢንተር በሜዳውና በደጋፊው ፊት የመልሱን ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ሰፊ የማለፍ እድል ያለው ኢንተር ሚላን የዛሬውን ጨዋታ ድል አድርጎ ግማሽ ፍጻሜውን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ዕትም
Next articleሊጉን በ2ኛነት የሚመራው ባሕርዳር ከተማ ዛሬ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ይጫወታል።