“የሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

72
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚንስትር ፒተር ሲያርቶ ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በዛሬው ዕለትም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነቶችን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ከሀንጋሪ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚንስትር ፒተር ሲያርቶ ጋር ስኬታማ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
በ1956 ዓ.ም የተጀመረውን የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማዳበር በሚያስችሉ ጉዳዮች እንዲሁም በአካባቢያዊ እና በባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ነው ያነሱት።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ስለመግለፃቸውም ነው ቃል አቀባዩ የጠቀሱት።
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ችግር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ትግበራ በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጨባጭና ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚንስትር ፒተር ሲያርቶ በበኩላቸው በኢኮኖሚና በሲቪል አቪየሽን መስክ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት እንዲደረግ ላቀረቡት ጥያቄ ኢትዮጵያ ይሁንታ ማሳየቷንም አምባሳደር መለስ ጠቅሰዋል።
ሀንጋሪ በምትታወቅበት በውኃ ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎችም ትብብራቸውን ለማጠናከር መነጋገራቸውን አክለው ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጎለብት ሀንጋሪ ተገቢውን በጎ ሚና እንደምትወጣም ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
በሳምንቱ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት፤ ሀገሪቱ ከቀውስ ወደ ተሻለ ሰላም እና አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ ነው ብለዋል።
አምባሳደር መለስ አክለውም ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ የማስረዳት፣ የማለዘብና ወዳጅ የማብዛት ስትራቴጂን በተቀናጀ ሁኔታ እየተገበረች መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በጎረቤት ሀገራትና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት መስፈን የበኩሏን ሚና ለመወጣት ያላትን ሚና በተመለከተ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
የቀድሞው ኦስትሮ-ሀንጋሪ አካል የነበረችው ሀንጋሪ በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኝ ስትሆን ከኢትዮጵያ ጋር ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው በ1956 ዓ.ም ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleቢዝነስ ዜና: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም
Next articleአዲስ አበባ ስቱዲዮ ትዕይንተ ዜና: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ)