የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

238

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ከሕግ አስፈጻሚና አስተርጓሚ እንዲሁም ከሕዝብ ክንፍ መሪዎች ጋር እየተወያዬ ነው፡፡
በመድረኩ የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት አቶ ገረመው ገብረጻድቅ በሕግ ማስተዳደርና የሕግ የበላይነት ማስከበር የተለያዩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ መሪዎች በሕግ ከማስተዳደር ወጥተው የሕግ የበላይነት እንዲከበር እንዲሠሩ ያሳሰቡት አቶ ገረመው የሕግ የበላይነት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ደግሞ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ለሕግ ተገዥ በመሆን ሕግ እንዲያስከብሩ አሳስበዋል፡፡ ሕግን ማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ያመለከቱት አስተያዬት ሰጭዎቹ በየደረጃው ያለው ሕግ አስፈጻሚ ሕግ አክብሮ ሕግ ለማስከበር እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
በተለይ የመንግሥት መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ በትክክል ተግባርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተወያዮቹ አሳስበዋል፤ መንግሥታዊ አገልግሎት በየመሥሪያ ቤቱ በአግባቡ እየተሠጠ አለመሆኑ ለሕግ የበላይነት አለመከበር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልክተዋል፡፡
የመንግሥት ሕግን የማስከበር ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት መኖሩ በተወያዮቹ ተነስቷል፤ ‹‹የሕዝቡ ሥርዓት ያለው መሆንና ሃይማኖተኛነት ባያግዝ ኖሮ የሕግ ማስከበር ክፍተቱ ለከፋ ችግር የሚዳርግ ነበር›› ብለዋል ተወያዮቹ፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች የሕግ የበላይትን ለማስከበር ሁሉም የመንግሥት መዋቅር እስከታች ድረስ ተናብቦ እንዲሠራም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous articleአሜሪካ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የስልጣን መጋራት ጊዜውን መግፋታቸው እንዳሳሰባት ተናገረች፡፡
Next articleበቀወት ወረዳ የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡