“በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት አለን” የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ‘ሩስሃይድሮ’

86
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ‘ሩስሃይድሮ’ (RusHydro) በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎች ከሩስሃይድሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል የማምረት አቅም ቢኖርም የኢነርጂ አቅርቦቱ ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢነርጂ አቅርቦቱን ለማሳደግ እና በቀጣናው የተጀመረውን የኃይል ትስስር ለማስፋፋት ኢነርጂ የማምረት፣ የማሰራጨት እና የማስተላለፍ አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የኢነርጂ ፍላጎት እያደገ መሄድ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ኢነርጂ ማምረት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን እና ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ከውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የሩስሃይድሮ የሥራ ኃላፊዎች ለረጅም ጊዜ የቆየ የኃይል ማምረት እና የማሰራጨት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው፣ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኃይል ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
እ.አ.አ 2004 የተቋቋመው ሩስሃይድሮ በሩሲያ ከሚገኙ ግዙፍ የኤሌትሪክ ኃይል ኩባንያዎች አንዱ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ የሲቪል ሥራ 75 በመቶ ደረሰ።
Next articleስፖርት ዜና: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ)