የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ የሲቪል ሥራ 75 በመቶ ደረሰ።

169
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ ግንባታ የሲቪል ሥራ 75 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።
የፋብሪካው ግንባታ ከተጀመረ አራት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን ሲቪል ሥራው በመጪው ሰኔ ተጠናቅቆ ወደ ማሽን ተከላ እንደሚገባ ተገልጿል።
ፋብሪካው በመጀመሪያው ዙር በዓመት አምስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ያመርታል ተብሏል።
በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የተመራ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ቡድን የፋብሪካውን ግንባታ ሂደት ጎብኝቷል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።
ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ አሁን ላይ በሀገሪቱ በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋለውን የሲሚንቶ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀርፍ የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በጉብኝቱ ወቅትም ገልጸዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው፣ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ስኬታማ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ይሆናል ብለዋል።
የገቢዎች ሚንስትር ዓይናለም ንጉሤ ደግሞ የተጀመረው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
አሁን ላይ ሁለት ሺህ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አበባው በቀል ገልጸዋል።
ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ እንዲያመርት ዕቅድ ተይዞለት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ እየተገነባ የሚገኝ ትልቅ የሲሚንቶ ፕሮጀክት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
Next article“በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት አለን” የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ‘ሩስሃይድሮ’