
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) አሜሪካ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ስልጣን በመጋራት መንግሥት እንዲመሠርቱ የተደረሰበትን ስምምነት በቶሎ አለመፈጸማቸው እንዳሳሰባት ገልጻለች፡፡
በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ቲቦር ናጊ ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር (ዶክተር) የሕዝቡን ሠላም የመመለስ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በመዘግየቱም መጠየቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ረዳት ኃላፊው እንዳሉት አሜሪካ ሂደቱን እያጓተተ ያለውን በመለዬት ሂደቱን ለማፋጠን ግፊት ለማድረግ እየሠራች ነው፡፡ በታቀደው መሠረት ሁለቱ ኃይሎች ሕዳር 02 ቀን 2012ዓ.ም ጥምር መንግሥት ይመሠርቱ ነበር፤ ነገር ግን በቂ ዝግጅት እንዳልተደረገ በመግለጽ ከታቀደው በ100 ቀናት እንዲዘገይ ዩጋንዳ ላይ መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ የደቡብ ሱዳንን ሠላም የሚሹ ኃይሎች አልተደሰቱበትም፡፡
ደቡብ ሱዳን ራሷን ችላ ሀገር ከሆነች ከ2011 (እ.አ.አ) በኋላ ሠላም የተነፈሰችው ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር እና ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ቅራኔ ውስጥ ገብተው የእርስ በእርስ ጦርነት ተጀምሯል፤ እስካሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ለስደት ተዳርገው በኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳና ሌሎችም ሀገራት ይገኛሉ፤ በርካቶችም በእርስ በእርስ ግጭቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ