
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጎረቤት ሀገር ሱዳን ሕዝቦች ከጥንትም ጀምረው ነፃነታቸውን የሚወዱ እና ብሄራዊ ክብራቸውን አስጠብቀው የቆዩ ሕዝቦች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የሱዳን ሕዝብ ከሚወሳባቸው አያሌ መልካም ባህሪያት መሀከል ለጋስነት እና እንግዳ ተቀባይነታቸው ከምንም በላይ ጎልቶ ይጠቀሳልም ብለዋል ።
እነዚህ እሴቶች ደግሞ ከማኅበራዊ ትስስሩ በላይ የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ሕዝብ የሚያመሳስሉ እና ይበልጥ የሚያቆራኙ ብለውም ከሌላው እንዲለዩ ከሚያረጓቸው እውነታዎች ሁነው እናገኛቸዋለን።
በመሆኑም የሱዳን ሕዝብ በባህሪው ኩሩ በመሆኑ በምንም ሁኔታ ክብሩን እና ነፃነቱን አሳልፎ የሚሰጥ አያደርገውም።
ስለሆነም የሱዳን ሕዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት ታላቅ ዓቅም እና ጥበብ ያለው ታላቅ ሕዝብ በመሆኑ ማንኛውም የሁከት ዓላማን ያነገበ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያስተናግድ አይሆንም ብለዋል።
ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህ ኩሩ የሱዳን ሕዝብ አሁን ላይ እየገጠመው ያለውን ቀውስ በጥበብ ሊወጣው ይችላል ስንል ያለንን ፅኑ እምነት ለመግለፅ እንወዳለን ሲሉ ገልጸዋል።
የሱዳን ሕዝብ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ መተው ያለበት ሲሆን የማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓላማም ሰላምን እና ድርድርን በተመለከተ ብቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከዛ ውጭ በሆነ በማንኛውም ድብቅ አጀንዳ የተነሳሳ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ በታሪክ ሸንጎ ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ ይሆናል ሲሉ በመልዕከታቸው አስፍረዋል ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ በበኩሉ የሱዳን ሕዝብ የውስጥ ችግሩን በለመደው ጥበባዊ አካሄድ በራሱ እንዲፈታ የሚመኝ እና የሱዳን ሕዝብ ጥቅም ተከብሮ ማየት ትልቁ ፍላጎቱ መሆኑን ገልጸው፣ በህገወጥ መልኩ በሀገሪቷ ውስጣዊ ችግሮች ወስጥ እጁን የሚሰድን ማንኛውም የውጭ ኃይልን በፅኑ እንቃወማለን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!