ለይለተል ቀድር ቁርዓን የወረደባት ሌሊት በመሆኗ በዚች ሌሊት የተደረገ መልካም ነገር ከአንድ ሺህ ወር በላይ የበለጠ ዋጋ እንዳለው የእምነቱ አባቶች ተናገሩ።

103
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የወሮች ቁንጮ የሆነውና ታላላቅ ችሮታዎችን ጠቅልሎ የያዘው የረመዳን ወር ሊገባደድ ጥቂት ቀናቶች ይቀሩታል፡፡ ታላላቅ ትሩፋቶችን አዝሎ በአምላክ ፀጋዎች ደምቆ የአማኞቹን ልብ በብርሃኑ ሞልቶ በክብር ሊጠናቀቅ ወደ መጨረሻወቹ ቀናት ላይ እንገኛለን፡፡
ረመዳን የእዝነት፣ የምህረትና ከእሳት ነፃ መውጫ ወር ነው። በዚህ ወር ብዙ ስጦታዎችና ልግስናዎች ይጎርፋሉ።
ረመዳንን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ፣ የፍትሕ፣ የዕዝነት፣ ይቅርታንና ወደ ጀነት መቃረቢያ ልዩ ወር ነው፡፡
የቲሞችን የረዳ የተንከባከበ ነገ የውመል ቂያማ ሁለት ጣት ያክል እርቀት ነው የሚሉት የሃይማኖት አባቶቹ የረመዳን ጾም በመረዳዳት በመደጋገፍና ያለው ለሌለው በማካፈል መጾም እንደሚገባ ተናግረዋል። ጾሙ ከምግብና ከውኃ መከልከል ብቻ ሳይሆን መልካም ነገሮችን በማድረግ ጭምር እንደሚጾም አቶ አማን አብዱልዋህብ ነግረውናል።
ለይለተል ቀድር፣ በረመዳን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት የሚገኝ ቀን ሲሆን በእርሱም ቁርዓን ከለውሃል መህፉዝ ወደ በይተል ኢዛ በአንድ ጊዜ ተጠቃሎ የወረደበት ስለመሆኑም አስገንዝበዋል። በዚች ሌሊት የተደረገ መልካም ነገር ከአንድ ሺህ ወር በላይ የበለጠ ዋጋ እንደሚያስገኝም ነው የሚያብራሩት፡፡
ሌላው የእምነቱ አባት ዶክተር ኑረዲን ቃሲም በለይተል ቀድር የሚደረጉ የሃይማኖት ክንዋኔዎች ካለፉት ቀናት በበለጠ መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል። መስገድና ሌሎች የእስላምና ሥርዓቶችን በትጋት መፈጸም እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት፡፡
በኛ አዕምሮ የረጅም ዘመን እቅድ በፈጣሪ ደግሞ የአጭር ጊዜ እቅድ ሲሆን በለይለተል ቀደር ልክ ዓመታዊ እቅድ እንደምንለው የዓመቱ ሁለንተናዊ ወሳኔ የሚወሰንበት ነውም ብለዋል።
ዶክተር ኑረዲን የቀጣዩ ረመዳን ድረስ በህይዎት የሚቆዩ፣ የማይኖሩና የፍጥረታት የዓመት ሁነቶችና ክስተቶች የሚመነዘሩበትና የሚወሰንበት ቀን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየትንሣዔ በዓል በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሰላም ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
Next article“የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ