የትንሣዔ በዓል በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሰላም ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

63
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ2015 ዓ.ም የትንሣዔ በዓል በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሰላም ተከብሮ መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ደባልቄ ለአሚኮ ገልጸዋል።
ረዳት ኮሚሽነሯ በበዓላት ወቅት የተለያዩ ወንጀሎች፣ የትራፊክ አደጋዎች እና የእሳት አደጋዎች የሚጠበቁ ናቸው ብለዋል።
የትንሣዔ በዓል በሰላም እና በተረጋጋ መልኩ እንዲከበር የክልሉ ፖሊስ በእቅድ የሚመራ የወንጀል እና አደጋዎችን መከላከል ሥራ እያከናወነ እንደነበር ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ብቻ መጠነኛ የትራፊክ አደጋ መድረሱን የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነሯ ሌላ ምንም አይነት አደጋ እና ወንጀል በክልሉ እንዳልተፈጸመ ነግረውናል።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከፖሊስ የቅድመ መከላከል ዝግጅት በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ገልጸዋል።
“ማኅበረሰባችን ከጸጥታ አካላት ጎን በመኾን ሰላሙን የማስጠበቅ ጠንካራ እሴት አለው” ያሉት ረዳት ኮሚሽነር መሰረት የሰላም ዘብ ለኾኑ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይነትም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል በፍጹም ሰላም እና መረጋጋት ለማክበር ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።
የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሣዔን በዓልን ተረጋግተው እንዲያከብሩ የእስልምና እምነት ተከታይ እህትና ወንድሞች አካባቢያቸውን በንቃት የመጠበቅ ሥራ እያከናወኑ ነበርም ብለዋል።
ይህ አይነት የመተሳሰብ እና በጋራ ቁሞ ሰላምን የማስጠበቅ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከማንኛውም የፕላስቲክ አይነቶች ነዳጅ በመፍጠር ለዕይታ አቀረበ።
Next articleለይለተል ቀድር ቁርዓን የወረደባት ሌሊት በመሆኗ በዚች ሌሊት የተደረገ መልካም ነገር ከአንድ ሺህ ወር በላይ የበለጠ ዋጋ እንዳለው የእምነቱ አባቶች ተናገሩ።