የደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከማንኛውም የፕላስቲክ አይነቶች ነዳጅ በመፍጠር ለዕይታ አቀረበ።

72
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ንድፈ ሃሳብን ከተግባር አዋህደው በማስተማር፣ በማሰልጠንና በሥነ ምግባር በማነጽ ወጣቶችን ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ የቴክኖሎጅ ሽግግር በማድረግም ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና ይጫዎታሉ፡፡
የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም ይህንኑ ተልዕኮ በመያዝ ወጣቶችን በሙያና ቴክኒክ በማሰልጠን ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን እያፈራ ነው፡፡
በደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን የምርት ዘርፍ አሥተባባሪ መልካሙ ታደሰ ኮሌጁ ከማንኛውም ፕላስቲክ አይነት ነዳጅ በማምረት ለዕይታ አቅርቧል ብለዋል፡፡ አገልግለው የወዳደቁ ማንኛውም የፕላስቲክ ዕቃዎች ነዳጁን ለማምረት በግብዓትነት መጠቀማቸው አካባቢን ከብክለት ነጻ ከማድረግ ፖሊሲ ጋር የሚስማማ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የሚመረተው ነዳጅ የኬሚካል ይዘቱን በዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዲቀመር መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡
ፈጠራው አካባቢ የሚያቆሽሸውን ፕላስቲክ ለማስወገድና ነዳጅን ተክቶ በመጠቀም ለምጣኔ ሐብት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር የሥራ ሂደት የቴክኖሎጂ ዘርፍ አስተባባሪ ሞገስ ጌታነህ በምርምር ውጤቱ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲችሉ አስቀድሞ የማለማመድ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ምክትል ዲን እና ተወካይ ዲን ክንዴ ጌታሁን ኢትዮጵያ ካላት ሃብት ውስጥ አንዱ የሰው ሃብት መሆኑንና ይህንን ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂም አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ያሉት አቶ ክንዴ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚስማማ ነዳጅም መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ ሃሳብ ስለመኖሩም ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፦ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ወገን በተግባር የተገለጠ አለኝታነቱን አሳይቶናል” በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች
Next articleየትንሣዔ በዓል በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሰላም ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።