ወጣቶች የመቻቻልና የመረዳዳት መልካም እሴቶች ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ተጠየቀ።

96

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ እና መቅደላ የባሕል ቡድን የትንሣዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ 1 ሺህ በላይ ለሚኾኑ አቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት አካሂደዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው የመረዳዳት ባሕል አንዱ ሃይማኖታዊ እሴት በመኾኑ በዓሉን ስናከብር አቅም የሌላቸውን በማገዝ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የበጎ አድራጎት ሥራ እየጎለበተ መምጣቱን ያነሱት ኀላፊው የመቅደላ የባሕል ቡድን የአካባቢውን ባሕል ከማጎልበት ባለፈ ለአቅመ ደካሞች እያደረገ ያለው ድጋፍ አንዱ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የመቻቻልና የመረዳዳት ባሕል እንዲያድግ ለሚሠሩ አካላት ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ሌሎች ወጣቶችም መልካም እሴቶች ማጎልበት ሥራ ላይ አተኩረው እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የመቅደላ ባሕል ቡድን ሥራ አስኪያጅና አሰልጣኝ ዮናስ ዳኘ እንዳሉት የባሕል ቡድኑ የአካባቢውን ባሕል ከማስተዋወቅ ባለፈ ላለፉት ስድስት ዓመታት የትንሣዔ በዓልን መሠረት በማድረግ ከማኅበረሰቡ ሀብት በማሰባሰብ ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት ሲሠራ ቆይቷል። በዚህ ዓመትም ከ1 ሺህ 200 በላይ አቅመ ደካሞች ማዕድ ለማጋራት ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም መልካም እሴት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ትንሣዔስ መቼ ነው?
Next articleበኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የትንሣኤን በዓል አከበሩ።