
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአምላክ ስም በሰርክ የሚነሳባት፣ ምስጋና የሚቀርብባት፣ ለምድር የተሰጡ ስጦታዎች ያሉባት፣ ደጋጎች የሚወለዱባት፣ ጤዛ እየላሱ፣ ድንጋይ እየተንተራሱ የሚኖሩባት የኢትዮጵያ ትንሣዔስ መቼ ነው?
ገና በጥንት ዘመን ለድል መታሰቢያ ሐውልት ያቆመችው፣ ቤተ መቅደስ ጨርሳ የጀመረችው፣ ጣሪያ ሠርታ መሠረት ያወጣችው፣ ከአንድ ዓለት ላይ አብያተ ክርስቲናትን የቀረጸችው፣ ጡብ ደርድራ እጅግ የተዋበ ቤተ መንግሥት ያነጸችው፣ ደብር የደበረችው፣ ገዳም የገደመችው፣ ፊደል የቀረጸችው፣ ብራና ፍቃ ቀለም በጥብጣ ታሪክ የከተበችው፣ በነጻነት የኖረችው፣ በታሪክና በእሴት ከፍ ከፍ ያለችው፣ ለጠላቶቿ እሳት የሆነችው ኢትዮጵያስ ትንሣዔዋ መቼ ነው?
የደፈሯትን የቀጣችው፣ የገፏትን የጣለችው፣ ጦር ያዘመቱባትን ዘማቾቹንም አዝማቾቹንም ያሳፈረችው፣ ለዘመናት በጀግና ልጆቿ የተጠበቀችው፣ ለምስክርነት የተቀመጠችው፣ አብዝታም የተወደደችው፣ የነጻነት ምልክት የሆነችው፣ ኢትዮጵያ ትንሣዔዋ መቼ ነው?
እጅግ የረቀቁ ምስጢራት ያሉባት፣ ያልተመረመሩ ታሪኮች የመሉባት፣ ጠላቶች የሚርዱ የሚንቀጠቀጡላት፣ አንገታቸውን አዘንብለው የሚንበረከኩላት፣ ተስፋ ያጡት ተስፋ የሚያደርጓት፣ የተቅበዘበዙ የሚጽናኑባት፣ የተራቡ የሚጎርሱባት፣ መድረሻ ያጡ የሚጠለሉባት ኢትዮጵያ ትንሣዔስ መቼ ነው? ቂምና ጥላቻ በርክተውባታል፣ መጠላለፉ አይሎባታል የስቅለቱ ቀን ረዝሞባታልና፡፡ ስቅለቷ ለቀናት አይደለም፣ ለሳምንታትም አይደለም፣ ለወራትም አይደለም፣ ለዓመታት ሆነባት እንጂ፡፡ የሚገፏት በዝተዋል፣ የሚያዳፏት አይለዋል፡፡
በዘረኝነት፣ በጥላቻ፣ እኔ ብቻ ልጥገብ በሚል እሳቤ፣ በመንደርተኝነት፣ በመጠላለፍ፣ በአለመተማመን፣ በመገፋፋት ተወጥራለች፣ ሰላም በማጣት ችንካር ተቸንክራለች፣ ፍቅር በጠፋበት ቀን ቆማለች፡፡ እርሷ በእውኑ ትንሣዔን አብዝታ ትሻለች፡፡
ታሪክ ያገነናት፣ ደምና አጥንት ያጸናት፣ ምስጋና ውዳሴ የማይለይባት፣ ጦር አዝምተውባት ያልተሸነፈችው፣ ሁሉንም ድል አድርጋ ዘመናትን የተሻገረችው ኢትዮጵያ የስቅለቱን ዘመን ማለፍን ትሻለች፡፡
በጸና አንድነቷ፣ በጠነከረ ጀግንነቷ፣ በአትንኩኝ ባይነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ግን ትንሣዔን ትሻለች፡፡ ዘረኝነት አጉብጧታል፣ ክፋትና ምቀኝነት፣ ጥላቻና ቂም መከራዋን አጽንቶባታል፣ በአርብና በእሑድ፣ በስቅለትና በትንሣዔው ያለውን ዘመን አርዝሞባታል፣ የጨለማ ዓመታት በዝተውባታል፡፡
ኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ መቃኘት ከጀመረችበት ዘመን ጀምሮ ንፁሐን በግፍ አልፈዋል፣ በሚወዷት ኢትዮጵያ ቤታቸው እንዳሻቸው እንዳይኖሩ ተከልክለዋል፣ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ በረሃብና በጥም፣ በዝናብ እና በፀሐይ ተሰቃይተዋል፡፡ ሰውነት እንጂ ማንነት በማይቆጠርባት ጥንታዊት ሀገር ማንነት እየተመዘዘ፣ ሰውነት እየደበዘዘ ብዙዎች በግፍ አልፈዋል፡፡ ብዙዎች ዛሬም ቀያቸውን ናፍቀዋል፣ በቤታቸው ውለው ማደርን እንደ ሕልም በአሻገር ሆነው ተመልክተዋል፡፡ በችግር ውስጥ ሆነው ነገን ናፍቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ልኳ አንድነት፣ ጽናት፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና ከራስ በፊት ለወገኔ የሚል ሆኖ ሳለ ዛሬ ላይ ከልኳ የሚያሳንስ ዘረኝነት፣ መንደርተኝነት እና ለወገኔ ከማለት ይልቅ ለራስ የሚል ጥቅመኝነት ፈተናዋን አብዝተውባታል፡፡ ስቅለቷን አርዝመውባታል፡፡ ለተስፈኞች ዛሬ ካለች ጨለማ ነገ ያለች ብርሃን ትበልጣለች፡፡ ለምን ካሉ ነገ ያለችው ብርሃን ለዘላለም ታበራለች፣ ዛሬ ያለችውም ጨለማ ለዘላለም ትጠፋለችና፡፡
ስቅለት ካለ ትንሣዔ አለ፡፡ በስቅለት የተጨነቁት ሁሉ በትንሣዔው ይደሰታሉ፣ በትንሣዔው ከወገኖቻቸው ጋር አንድ ይሆናሉ፣ በትንሣዔው ማቅ አውልቀው ያማረውን መብሩቅ ይደርባሉ፣ በትንሣዔው ባርነትን ጥለው ነጻነትን ይቀዳጃሉ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያስ ክፉዎች ያመጡባት ስቅለት፣ የመወጋትና የመድማት ዘመን የሚያልፍላት ትንሣዔዋ የሚመጣላት መቼ ይሆን?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ትንሣዔ እንዴት ኾኖ ይመጣል? ባልኳቸው ጊዜ ፈላስፋው እንደተናገረው ትንሣዔዋም ሞቷም በእጃችን ነው ያለው፤ አንድ ሰው ለአንድ ፈላስፋ ወፍ በእጁ ጨብጦ ሞታለች ወይስ አልሞተችም አለው፡፡ ሞታለችም ቢለው ይለቃታል፤ አልሞተችም ቢለው ተጭኖ ይገድላታል፡፡ ፈላስፋውም ሕይወቷም ሞቷም በእጅህ ነው አለው፡፡ የኢትዮጵያ ትንሣዔ በኢትዮጵያውያን እጅ ነው፤ የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳናስገባ፣ ኢትዮጵያውያን ተመካክረን ትንሣዔዋን ማቅረብ እንችላለን ነው ያሉኝ፡፡
በየዘመናቱ ችግሮች ተፈጥረዋል፣ አበው ግን የችግሮች መፍቻ ቁልፎች ነበሯቸው፤ ለሽማግሌ የሚተወው ለሽማግሌ ይተዋል፣ ለምሁራን የሚተወው ለምሁራን፣ ለሃይማኖት አባቶች መሰጠት ያለበት ለሃይማኖት አባቶች ይሰጣል በእነዚህ የችግሩ ቁልፍ ይገኛል፣ ችግሩም ይፈታል፤ እነዚህ ግዴለሽ እንዳንሆን መከላከያ ኀይሎች ናቸውም ይሏቸዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች ችግሩን ዳስሰው ከአንተ ላይ አይቸብሃለሁ ይላሉ፤ ችግሩ ይፈታ ዘንድ አንተ ተው ይላሉ ጥፋተኛውን፣ የሃይማኖት አባቶች ገዝተናል እስከማለት የሚደርስ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስልጣን አላቸው፣ ችግር ያዩበትን አቁም ይላሉ ችግሩም በእነዚህ ቁልፎች ይፈታል ነው ያሉት፡፡
እንደተሰቀለ የሚቀር የለም፤ አምላክ ፈተናን ይለውጣል፣ መከራን ያሳልፋል ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣዔ ከተማርን ጥላቻን እናሸንፋለንም ብለውኛል፡፡ ጥላቻን እንጣል፣ ችግሮቻችንን ተወያይተን እንፍታ ነው የሚሉት፡፡ ጉልበታሞች ሲጋጩ ደኃዎች፣ ሕጻናት፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አዛውንቶች ይጎዳሉም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የችግሮች መፍቻ ብዙ ልምዶችና ቁልፎች እንዳሏት ያነሱት ብፁዕነታቸው የራስ ወርቅ አያደምቅ እንዲሉ የሌላ በዓድ ሸክም ካልመጣ በስተቀር እኛ በእኛ ችግር የመፍታት አቅም ተሟጦ ያለቀለት መስለናልም ነው ያሉት፡፡ ከትናንት ችግሮች እንማር፣ በትናንት ችግሮች ብዙዎች ሞተዋል፣ ብዙዎች በሀዘን አለንጋ ተገርፈዋልና፡፡ ከጥልና ከጥላቻ ያተረፈ የለም፣ ሰላምን ገንዘብ እናድርግ ነው ያሉት፡፡ ለሰላም ዘብ እንቁም፣ እልህንና ጥላቻ የነገሰችባትን አንደበት እንተውም ብለዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ፍቅርን እናንግስ፣ ጥላቻን እንተው አንድ ሆነን ለሀገራችን እንሥራም ነው ያሉት፡፡ መልካም ሥራ ከሠራን ትንሣዔ ልቡና አለን፤ መልካም ካልሠራን ግን ሞታችን ያረጋገጥን፣ በቁም የሞትን ሙታን እንባላለን ነው ያሉኝ ብፁዕነታቸው በመልሳቸው፡፡
አዎን አንድነትን፣ ጽናትን፣ አብሮነትን እና ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደምን ጊዜ የኢትዮጵያ ስቅለት ያበቃል፣ ትንሣዔዋም ይመጣል፣ ደስታውና ሰላሙም ከፍ ይላል፡፡
በታርቆ ክንዴ