
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች በጦርነት ምክንያት ለሦስት ዓመታት ከቀያቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ መቆየታቸው ይታወቃል። ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ሳይቀር ወረዳው ነጻ ሆኖ ነዋሪዎች ወደቀያቸው ተመልሰው የቀደመ ልማታቸውን ማከናወን አለመቻላቸው ለድርብርብ ችግር ዳርጓቸው መቆየቱን አሚኮ በተከታታይ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።
በቅርቡ ወረዳው ነጻ በመኾኑ ነዋሪዎች ወደየቀያቸው ተመልሰዋል። ያነጋገርናቸው ወገኖችም ወደ ቀያቸው መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸውልናል። ጥለውት የሸሹትን ቤትና ንብረት እንደነበረ ባለማግኘታቸው ግን ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
አቶ ደባሽ ክንዱ የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪ ሲኾኑ ከሦስት ዓመታት በላይ ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደቆዩ ነግረውናል። አሁን ላይ ወረዳው ነጻ ኾኖ ወደቀያቸው ተመልሰው በቤታቸው በዓል እያከበሩ መኾኑ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል። “ለወትሮው የነበረው የበዓል ዝግጅት አሁን ላይ ባይኖርም፣ ባለን ነገር ተደስተን ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለመዋል ዝግጁ ነን” ሲሉም ተናግረዋል።
ጥለውት የሄዱት ሀብትና ንብረት በሙሉ ወድሞ ያገኙት አቶ ደባሽ ወደ ቀድሞው የልማት ሥራቸው ለመመለስ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ሌላው ነዋሪ አቶ ብርሃኑ አበበ ወደቀያቸው ከተመለሱ ሳምንት ሞልቷቸዋል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በዓልን በቤታቸው ማክበራቸው እንዳስደሰታቸውም ነግረውናል። “በርካታ ጎደሎዎች ቢኖሩበትም፣ ለወትሮው ብዙ የደስታ በዓላትን ወዳሳለፍንበት ቤታችን ተመልሰን ስለገባን ደስ ብሎናል” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ጊዜያዊ እርዳታ መቅረብ ነበረበት ብለዋል። ወደ ቀያቸው ቢመለሱም የዕለት ደራሽ እርዳታዎች ግን በበቂ ሁኔታ እየደረሱ እንዳልኾነ ተናግረዋል።
የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ አበርገሌ ወረዳ ነጻ እንደኾነ ነዋሪዎቹን የመመለስ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ይሁን እንጅ በቤታቸው ምንም አይነት ደራሽ ምግብ እንደሌለ እና ረጅ ድርጅቶችም ተከታትለው እንዳልገቡ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ምህረት ገለጻ በቁጥር ከዘጠኝ በላይ ከሚደርሱ ረጅ ድርጅቶች ጋር ንግግር በማድረግ ሕዝቡ እርዳታ እየጠበቀ ስለመኾኑ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል። ይሁን እንጅ የእርዳታ እህል ለማድረስ እንቅስቃሴ የጀመረው ኤፍ ኤች ኢትኖጵያ ብቻ ነው ብለዋል። የኤፍ ኤች ኢትዮጵያ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎችም በወረዳው ሙሉ በሙሉ ሰላም አልሰፈነም በሚል ስጋት የጫኑትን እርዳታ ይዘው እንደቆሙና ገና ወደ ወረዳው እንዳልገቡ አቶ ምህረት ገልጸዋል።
አካባቢው ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን በማሳወቅ እርዳታ ጭነው የቆሙ መኪናዎች እንዲገቡ ውይይት እየተደረገ ስለመኾኑም አቶ ምህረት ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ተፈናቅለው ከቆዩበት ሕይወት ተመልሰው በዓልን በቤታቸው ማሳለፋቸው መልካም ቢኾንም ምንም አይነት የዕለት ደራሽ እርዳታ አለመኖሩ አሳሳቢ መኾኑንም ገልጸዋል።
በመኾኑም መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ርብርብ በማድረግ ነዋሪዎች የዕለት ደራሽ እርዳታ የሚያገኙበትን እና በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!