
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሞት አቅም አጥቷል፣ አስፈሪ እንዳልነበር እርሱ ራሱ ፈርቷል፤ ጌታን መያዝ አቅቶታል፣ ደንግጧል፣ ርዷል፤ ተንቀጥቅጧል፤ ብርሃን ከሰማይ መጥቷል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ ተነስቷል፣ መግነዝ አልተፈታለትም፣ መቃብርም አልተከፈተለትም፣ ሁሉንም በራሱ ኃይልና ስልጣን አደረገ እንጂ፡፡
ከትንቢት አልዘገየም፣ ከትንቢትም አልፈጠነም፣ ሁሉንም በጊዜው አደረገ፡፡ ነብያት የተነበዩለት፣ ነፍሳት ተስፋ ያደረጉት፣ የነፋስ አውታራት የሚታዘዙለት፣ ቀላያት የሚደነግጡለት፣ ሰማይና መሬት የማይወስኑት፣ ዘመናት የማይቆጠሩለት፣ ስለ ክብሩ ለመጻፍ ሰማይና ምድር ተጠቅልለው ብራናዎች ቢሆኑ የማይበቁት፣ በክረምት የሚፈስሱት ማዕበላት፣ ከዓመት እስከ ዓመት የሚወርዱት አፍላጋት፣ ምድርን የሚከቧት ውቅያኖሶች፣ ባሕሮዎች እና ሐይቆች ቀለማት ቢሆኑ የማይችሉት ኃያል አምላክ ተነስቷል፡፡
በተሰቀለ ጊዜ ከዋክብት የረገፉለት፣ መጋረጃዎች የተሰነጣጠቁለት፣ ቀንም አይደለም ሌሊትም አልነበረም እንደተባለ ፀሐይ ስለ ክብሩ ብርሃኗን የከለከለችለት፣ ጨረቃም ደም የለበሰችለት፣ መላእክት ከሰማይ እስከ ምድር እየረበቡ የሚታዘዙለት፣ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት፣ ክንፋቸውን እያማቱ ለክብሩ የሚፋጠኑለት፣ ሰማዕታት ስለ ፍቅሩ ሞትን የሚንቁለት፣ ጻድቃን፣ ደናግላን፣ ስሙን እየጠሩ የሚያመሰግኑት፣ ሐዋርያት ዓለምን እያካለሉ ያስተማሩለት ቅዱስ አምላክ በኃይሉና በሰልጣኑ ተነስቷል፡፡
በሕቱም ድንግልና የተጸነሰው፣ በሕቱም ድንግልና የተወለደው፣ በሕቱም መቃብር ተነስቷል፣ መቃብርን ባዶ አስቀርቷል፤ እንደርሱ ሆኖ የተጸነሰ አልነበረም፣ እንደርሱ ሆኖ የተጸነሰ የለም፣ እንደርሱ ሆኖ የሚጸነስ ለዘላለም አይኖርም፣ እንደርሱ ሆኖ የተወደለ አልነበረም፣ እንደርሱ ሆኖ የተወለደ የለም፣ እንደርሱ ሆኖ የሚወለድ ለዘላለም አይኖርም፣ እንደርሱ ሆኖ የተነሳ አልነበረም፣ እንደርሱ ሆኖ የተነሳ የለም፤ እንደርሱ ሆኖ የሚነሳ አይኖርም፡፡ እርሱ የማይመረመር ረቂቅ ነውና፡፡
መቃብር ጠባቂዎች አላስቀሩትም፣ ሞትም፣ ገዳዮችም አልያዙትም፣ ሁሉንም አሸነፋቸው፣ ድል መታቸው እንጂ፡፡ በጌታዋ መሰቀል የጨለመች ፀሐይ ብርሃኗን ሰጥታለች፣ ደም የለበሰችውም ጨረቃ ደስ ተሰኝታለች፣ ጨለማዋ ሲኦል በብርሃን ተመልታለች፣ በግዞት የያዘቻቸውን ነፋሳት ተነጥቃለች፣ በተስፋ የጠበቁት ነፍሳት ጌታቸው መጥቶላቸዋል፣ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶላቸዋል፣ ሲኦልን በርብሮ ነጻ አውጥቷቸዋል፣ የጨለማውን ካባ አውልቆ የማያረጅና የማይጠወልገውን ብሩህ ልብስ አልብሷቸዋል፤ ጠላተ ዲያቢሎስን አስሮላቸዋል፡፡
ወዮለት ለከዳው፣ ወዮለት ለሸጠው፣ ወዮላቸው በጦር ለወጉት፣ ወዮላቸው ላዳፉት፣ ወዮላቸው ለገፉት፣ ወዮላቸው የሕይወት ውኃ የሚያጠጣውን ጌታ መራራ ሃሞት ላጠጡት፣ ወዮላቸው እጅና እግሩን ለቸነከሩት፣ ወዮላቸው የእሾህ አክሊል ለደፉበት፣ ወዮላቸው ለገረፉት፣ ወዮላቸው የሞት ፍርድ ለፈረዱበት፣ ወዮላቸው ለወገሩት፣ ወዮላቸው ላስወገሩት፣ ወዮላቸው በምድር ላይ ለጎተቱት፣ ወዮላቸው መስቀል አሸክመው መከራውን ላጸኑበት፣ ወዮላቸው ለተዘባበቱበት፣ ወዮላቸው ለተፉበት፣ ወዮላቸው በጥላቻ ለተመለከቱት፣ ወዮላቸው በክፋት ለነኩት፣ ወዮላቸው በሀሰተኞች አደባባይ ላቆሙት፣ ወዮላቸው ቅዱስ ሳለ እንደ ሐጥያአተኛ ለቆጠሩት፣ ወዮላቸው በርባን ይፈታ ክርስቶስ ይሰቀል ላሉት፣ ወዮላቸው በሞቱ ለተደሰቱት፣ ወዮላቸው ተፈፀመ ባለ ጊዜ ሞቶ ይቀራል ብለው ሀሴትን ላደረጉት፡፡ እርሱ ተነስቷልና የት ይገባሉ? እርሱ ሞትን በሞቱ ገድሏልና የት ይደርሳሉ? እርሱ ማንም ምንም የማያሸንፈው አምላክ ነውና ምን ይላሉ?
በስቅለቱ የደነገጡት በትንሣዔው ሲጽናኑ፣ በስቅለቱ የተደሰቱት በትንሣዔው ደንግጠዋል፣ በስቅለቱ ያለቀሱት በትንሣዔው ተደስተዋል፣ በስቅለቱ የሳቁት በትንሣዔው አልቅሰዋል፤ በስቅለቱ የዘበቱት በትንሣዔው አፍረዋል፣ አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡
እነዚያ የሕማማት ቀናት አልፈዋል፣ ዋይታዎች እና ለቅሶዎች በደስታ ተቀይረዋል፣ ደረት መድቃቱ፣ በዘሀን መቃተቱ፣ እንባ ማፍሰሱ፣ ድንጋይ መንከሱ ቀርቷል፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተነስቷልና፡፡
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባዔያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ ከትንሣዔው በፊት ሕማም ነበረ፣ ከሕማም በኋላም ትንሣዔ አለ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕመምም አንደበቶች የማይገልፁት፣ ሊነገር የማይቻል ጥልቅ ነው ይላሉ፡፡ አዳምና ልጆቹ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የተቀበሉትን መከራ ካሳ ሊከፍል የመጣ ነውና በዲያቢሎስ ፊት ለደረሰብን ስቃይ፣ በአይሁድ ፊት ካሳ ከፍሎልናል ነው የሚሉት ሊቁ፡፡
የዲያቢሎስን ዳኝነት በጲላጦስ ዳኝነት እንመስለዋን፣ ጌታ በጲላጦስ ፊት እንደቆመ ሁሉ አዳምም በዲያቢሎስ ፊት ቆሟል፣ አዳምና ልጆቹ በሲኦል የተገረፉትን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ተገርፎ ካሳ ከፈለላቸው፣ ካሳ ያስፈልገን ስለነበር ካሳ ከፍሎ አዳነን ነው ያሉኝ፡፡
ክርስቶስ እንደ ጻድቅ መስቀል ላይ ሆኖ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ይላል፣ እንደ አምላክነቱ ገነትን መስጠትና መንሳት ይችላልና በቀኙ የተሰቀለውን ገነትን ሲሰጠው በግራው የተሰቀለውን ገነትን ነሳው፣ በመስቀል ላይ ሆኖ ፍትሕን ይሰጥ ነበር፣ በመስቀል ላይ እያለም የእግዚአብሔር ምሕረት አልተለየችም፣ እየበደሉት አልበደላቸውም፣ እየሰቀሉት አልሰቀላቸውም፣ እርሱ ግን ታገሳቸው ዝም አላቸው ይላሉ ሊቁ፡፡
በመስቀል ላይ ፍትሕን፣ ፍቅርን፣ ትግዕስትን፣ ትሕትናን አስተማረ፡፡ እየጨከኑበት ራራላቸው፣ የአብ ምሕረት፣ የወልድ ትግዕስት፣ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነት አልተለየምና፡፡ እንደ አጠፉኝ ላጥፋቸው፣ እንደ በደሉኝ ልበድላቸው አለማለትን በመስቀል ላይ አስተምሯልም ብለውኛል ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ፡፡
ክርስቶስ በሞቱ አድኗል፣ በሞቱ ለሰው ልጅ መልካምን አድርጓል፡፡ በተሰቀለ ጊዜ ከጎኑ በፈሰሱት ደምና ውኃ በውኃው እንጠመቅበታለን፣ ታጥበን ከሐጥያአታችን እንጠራበታለን፣ ያ ውኃ ከገነት ፈሳሾች የሚመረጥና የሚበልጥ ውኃ ነው፡፡ ቅዱስ ውኃ ከጎኑ ፈልቆልናል፣ ቅዱስ ደሙም ለመጠጣችን ሆኖልናል ነው ያሉት፡፡ ክርስቶስ ለሚወዱን ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉንም በጎ እናደርግ ዘንድ አስተምሯል ብለዋል፡፡
በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ነጻነትን ሰጣቸው፣ ከዲያቢሎስ እጅ ነጠቃቸው፡፡ እርሱ በተነሳ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ አላለም፣ ለምን ቢባል መለኮት የተዋሐደው ስጋ በመቃብር ነበርና፡፡ እርሱ በመለኮትነቱ ረቂቅነት ይስማማዋል፡፡ ጌታ ሲነሳ በመቃብር መግነዙን ጥሎ ወጣ፣ ያ መግነዝም ፍዳና መርገም ነው፤ ያም ፍዳና መርገም ለአዳም የቀረለት ነው፣ የመቃብሩ በዶ መሆን ወደ ገነት መግባታችን ማረጋገጫ ነው፣ የቀደመ ልብሳችንም ተመልሷል፤ ለዚያም ነው ክርስቶስ መግነዙን ጥሎ የወጣው ነው ያሉኝ፡፡
ጌታ በተነሳ ጊዜ ዓይኖች አይተው የማይችሉት ብርሃን ታየ፤ የጌትነቱ ምስጢር ኃያል ነውና አይሁድ ያን ብርሃን አላዩትም፡፡ ለወትሮው በመቃብር ዙሪያ ጥሩ ማዕዛ አልነበረም፣ በጌታ መቃብር ዙሪያ ግን ከማዕዛዎች ሁሉ የላቃ ማዕዛ ነበረ፡፡
የጌታን የመነሳት ብርሃን መላእክት አዩት፣ መግደላዊት ማርያምና ሌሎችም ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን አዩ፣ ምን አይነት መታደል ነው? ምን አይነትስ መመረጥ ነው? ከጭንቋ አርብ ወደ ደስታዋ እሁድ መድረስ፣ ምን አይነት መታደል ነው? በመከራዋ አርብ አልቅሶ በብርሃኗ እሁድ መደሰት፡፡ ሁሉም በእርሱ ኾነ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ ስለ ትንሣዔ ሲናገሩ ትንሣዔ ለክፉዎችም ለደጋጎችም መልእክት አለው፤ እንደ ክፉዎቹ እንደ አይሁድ ብትሆኑ ወድቃችሁ ትቀራላችሁ የሚል፣ ክፉ ብንሆን እርስ በእርሳችን መስማማት አይኖርም፣ እርስ በእርሳችን አንገባባም፣ ክፉ ብንሆን መቃብር ጠባቂ ሆነን ነው የምንቀረው፣ ለደጋጎቹ ደግሞ ምንም ጨለማ ቢበረታባቸው ትንሣዔውን ለማየት እንደማይቀር መልእክት አለው ነው ያሉኝ፡፡
ትንሣዔ እንዳለ እንመን ትንሣዔ እንዳለ ካመንን ምንም ጨለማው ቢበረታ ትንሣዔውን ከማየት አይከለክልም፣ ከትንሣዔ በኋላም ሞት የለም፡፡
እነሆ ክርስቶስ ተነስቷልና ደስ ይበላችሁ፣ እነሆ ሞትን ድል አድርጓልና ደስ ይበላችሁ፣ እነሆ ሞት ፈርቷል፣ ተንቀጥቅጧል፣ ሞቷልና ደስ ይበላችሁ፤ እነሆ የማያረጀው፣ በሰው እጅም ያልተሠራው የአዳም የክብር ልብስ ተመልሷልና ደስ ይበላችሁ፡፡ እነሆ ሲኦል ባዶዋን ቀርታለች፣ ዓለም በብርሃን ተመልታለች እና ደስ ይበላችሁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!