
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የትንሣኤ በዓል መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ከኃጢዓት ወደ ጽድቅ፣ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፣ ከአደፈና ከጎሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ማንነት የተሸጋገሩበት፣ ከበዓላት ሁሉ የበለጠ የነጻነት በዓል እንደኾነ አድርገው ያከብሩታል ነው ያሉት፡፡
ክብርና ነጻነት ለሰው ልጅ የተሰጡ የማይገሰሱ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ናቸው ያሉት አፈጉባዔው ሰው የመኾኑ መገለጫዎችና የሰብዕናው መሠረቶች ናቸውም ብለዋል፡፡
በውርደትና በባርነት የሚኖር ሰው ማንነቱን ያጣ፣ ሰብዓዊ ክብሩን የተቀማ፣ ያሻውን እንዳያስብና መሠረታዊ ፍላጎቶቹን እንዳያሟላ የተከለከለ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ያለነጻነት ሰውነት፣ ያለክብር ማንነት እንደማይኖር ጠቅሰው በክርስቶስ ትንሣዔ የሰው ልጅ ዘለዓለማዊ ጠላት የኾነው ሰይጣን ተሸንፏል ብለዋል፡፡
የሰው ልጅም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሩን፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከጉስቁልና ወደ ልዕልና መመለሱንም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አስከፊውን የጨለማ ዘመን ተሻግረው፣ የለውጥ አየር መተንፈስና የለውጡን ትሩፋቶች ማጣጣም ከጀመሩ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥረዋልም ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች ቢኖሩም ይህ ወደ ብልጽግና የሚያደርሰን ለውጥ እንዳይሰናከል፣ ብሎም ወደባርነት፣ ውርደትና ጉስቁልና እንዳንመለስ ሁሉም የበኩልን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የትንሣዔው ባለቤት የኾነው ክርስቶስ ከትንሣኤው አስቀድሞ በመዋዕለ ሥጋዌው ዓለም ንቆታል፤ ዘብተውበታልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሚናገራቸው ቃላት፣ የፈጸማቸው ተአምራት ሁሉ ተቀባይነት አልነበራቸውም ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ሁሉም ለውድቀቱ የሚኾን በትር አነሱበት እንጂ ጥብቅና አልቆሙለትም ብለዋል፡፡
እርቃኑን በቀራንዮ አደባባይ ላይ እንዲቆምና እንዲሰቀል አደረጉት እንጂ አልደገፉትም፤ ይሁን እንጂ በሞቱ ሞትን ድል ከነሳ፣ በመቃብሩ ትንሣዔውን ካወጀ ማግስት በኋላ ግን ብዙዎች አምላክነቱንና አስተምህሮውን አምነው ተከትለውታል ብለዋል።
የለውጥ ሀሳብ አፍላቂዎች ማኀበራዊ ቅቡልነት እስኪያገኙ ድረስ መከራው እንደሚበረታባቸው ጠቅሰው ሁላችንም ነገሮች ተፈጽመው ባስከተሉት ጥፋትና ውድመት ከመጸጸታችን በፊት አስቀድመን ግራ ቀኙን በአመክንዮ መመርመርና ማስተዋል ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ ላይ ነገን አሻግሮ ማየት እንደሚገባ፣ ዛሬ የምናጣጥለውና የምናቃልለው ሀሳብ የነገ መዳኛ ትልማችን ሊኾን ስለሚችል ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ወንድማማችነትና እኩልነትን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!