
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የብራዚል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉትን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ ጨምሮ በርካቶችን ሊፈታ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹን ከእስር ሊፈታ እንደሚችል የገለጸው ጉዳያቸው የፍርድ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በሚል ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን በዚሁ ካፀና ሉላ ዳሲልቫን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ብራዚላውያን ከእስር ይወጣሉ፡፡
ብራዚልን ከ2003 እስከ 2010 (እ.አ.አ) የመሩት ግራ ዘመሙ ዳሲልቫ ባለፈው ዓመት ነው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት፡፡ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ዳሲልቫ በክሱ ምክንያት ከፕሬዝዳታዊ ዕጩነት ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከእስር ቢወጡም በተወሰኑ መብቶቻቸው ላይ ግን መከሰሳቸው ብቻ ሊያግዳቸው እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ