“ኢትዮጵያ የቀደመ የታላቅነት ታሪኳን እንድታድስ በአራቱም ማዕዘን ያሉ ሕዝቦቿ ከመችውም ጊዜ በላይ ራሳቸውን እንደ ንስር አድሰው የሚነሱበት ወቅት ዛሬ ነው” አቶ ግርማ የሺጥላ

96
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ለትንሣዔ በዓል ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት ቀጥሎ ቀርቧል።
በቅድሚያ ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሳዔ በዓል በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
የአማራ ሕዝብ በፈተናዎች የበረታ ተግዳሮቶችን እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በብስለት የሚያልፍ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በወንድማማችነት የመልማት ፀጋን የሚጋራ አስተዋይ ሕዝብ ነው።
በአማራ ክልል ውስጥ የፖለቲካ ትግል ፍላጎታቸውን በፅንፈኝነትና በአመፅ ለማሳካት የሚሞክሩ ኃይሎች አማራን ማኅበራዊ ዕረፍት ከሚነሱ ልዩ ልዩ አካላት የተሰጣቸውን እርባና ቢስ የተላላኪነት ሚና ከመወጣት ያለፈ ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም ቅንጣት ያህል ፋይዳ የላቸውም፡፡
የአማራ ሕዝብ ለፍትሕ ርትዕ የሚተጋውን ያህል በስሙ በአውዳሚ የፖለቲካ ስልትና አመፅ ስልጣን ለመያዝ በሚደገፉት ኃይሎች የማይወከል ከመሆኑም በላይ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ኃይሎችን አምርሮ የሚታገል ሕዝብ እንደሆነ ቀደምት የፖለቲካ ትግሉ እና አስተምህሮቱ ያስረዳናል።
የብልጽግና ፓርቲ መሰረታዊ ዓላማን ለማሳካት ከሌሎች ወንድማማች ሕዝቦች ጋር ሁሉ ዓቀፍ ሀገራዊ ተሳትፎን በሁሉም ዘርፍ በማበልጸግ የኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ የአማራ ሕዝብ ትግል እና ተሳትፎ የጎላ ነው።
ብልጽግና ፓርቲ የጀመራቸውን በርካታ የእድገትና የለውጥ ምዕራፎች ከዳር ለማድረስ የሀገራችን ሰላም መሆን ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በሁሉም አካባቢ ሰላምን አስፍኖ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትጋት እየሠራን እንገኛለን።
ኢትዮጵያዊ አንድነት በየትኛውም ኃይል እንዳይፈተንና ይበልጥ እንዲፀና የአማራ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ የጎላ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል፡፡
የአባቶቻችን መንፈስ ታድሶ የአንድነት ችቦ ተለኩሶ ወደቁ ሲሉን ተነስተን አለቁ ሲሉን በዝተን ተበታተኑ ሲሉን ተሰባስበን እንደ አንበሳ በሚያስገመግም ድምፅ ኢትዮጵያን ከፍ አድርገን በመጥራት ለጠላቶቻችን ማቅ ለወዳጆቻችን ሸማ የምናለብስ ድንቅ ሕዝቦች ነን።
ኢትዮጵያ የቀደመ የታላቅነት ታሪኳን እንድታድስና የሕዝቦቿን የትስስር ገመድ አንድታጠብቅ በአራቱም ማዕዘን ያሉ ሕዝቦቿ ከመችውም ጊዜ በላይ ራሳቸውን እንደ ንስር አድሰው የሚነሱበት ወቅት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።
በመሆኑም ለምንሻት የበለፀገች ኢትዮጵያ ምስረታ ሰላም መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ወጣቱ፣ ምሁሩ፣ ፖለቲከኛው፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ አርሶ አደሩም ሆነ አጠቃላይ ሕዝባችን ለሰላም መኖርና መፅናት የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል፡፡
በአማራ ክልል ሕዝብ ውስጥ ያሉ የፀጥታ ስጋቶችን ከሌሎች ችግሮች ጋር አቀናጅተው እና ከልክ በላይ ለጥጠው የሽብርና የግጭት ሴራ በመጥመቅ የአራት ኪሎ መንበረ ስልጣንን ለመቆናጠጥ ቀን ከሌሊት የሚናወዙ ፅንፈኞች እኩይ ተግባር የማይሳካ ቅዠት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር አብሮ የወለደውን ስርዓት በፅንፈኛ ኃይሎች ከቶውንም ሊቀማ እንደማይችልም ማወቅ ይገባል፡፡
በአማራ ሥም እየማሉ እና እየተገዘቱ በሴራ ፖለቲካ ያልተገራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥማቸውን ጥም ለማርካት የቋመጡ ኃይሎች ሳይጀምሩት የመከኑ መሆናቸውን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ለማሳሰብ እንወዳለን።
በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የየቤተ ዕምነት አባቶች የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ያደረጉት ጥረት የሚመሰገን እና ለሰላም ያላቸውን ፅኑ አቋም እና ላበረከቱት የሰላም ጥሪ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
መላው ሕዝባችን እንደ መንግሥት ክፍተት ናቸው የሚላቸውን ችግሮች ሁሉ ነቅሶ በማውጣት በየጊዜው እንዲታረሙ በማድረግ በሌላ መልኩ ደግሞ እንደ ሕዝብ ለመቀጠል አደጋ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ያልተገሩ ፍላጎቶችና ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተጋምደን ለመኖር የማያስችሉ ዕኩይ ተግባራትን እና ፈፃሚዎችን በመከላከል ረገድ የአባቶቻችን ጥበብና ብልሃትን ተጠቅሞ የተሰራው ስራ ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ የሚሆን በመሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡
በቀጣይም እንደዚህ ዓይነት ከሚዛን ያልጎደለ እና ከአመክንዮ ጋር ያልተጣላ ተግባር እንደ ሀገር በህልውናችን ፀንተን ለመኖር ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ሊቀጥል የሚገባው በጎ ተግባር ነው፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ እንደ ሕዝብ የትኛውንም ህዝብ በጠላትነት አይፈርጅም፤ በጠላትነት የሚፈረጅ ህዝብም የለም፤ ነገር ግን እኩይ የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካት ሕዝብን እንደ መደበቂያ የሚጠቀሙ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል።
የአማራ ሕዝብ እሴቶች፣ ባህሎች እና የስነ መንግስት ታሪኮች የሚያሳዩት አቃፊነቱን ደጋፊነቱን ችግሮችን በሰከነ መንገድ የመፍታት ጥበብ ባለቤትነቱን በመሆኑ የትኛውንም አይነት ችግር ቢገጥመን እንኳ በድል እና በአሸናፊነት የምንወጣ ሕዝቦች መሆናችንን ታሪካችን ምስክር ነው።
የብዙ ሀገራት የወጣቶች ተሳትፎ ታሪክ የሚያሳየው መነሻቸውን ያወቁ የመዳረሻቸውን ትልም ያስቀመጡ በመሆናቸው ለድል እና አሸናፊነት መብቃት መቻላቸውን ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
በዚህ ረገድ የእኛ ሀገር ወጣቶችም ለምን ዓላማ ወደ አደባባይ እንደሚወጡ እና ኃላፊነቱንስ ማን እንደወሰደ ጠንቅቀው በማወቅ ከስሁት ትርክት አካሄዶች በመታረም ትግላቸውን ድህነትን ማሸነፍ አንድነትን ማበልፀግ ላይ ሊሆን ይገባል።
በዓይን ጥቅሻ መግባባት የሚችሉት ወጣቶቻችን ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለሀገርም ለትውልድም የሚጠቀም አሻራ ማሳረፍ ይገባቸዋል።
ዓለም ወደ አንድ መንደር በመጣችበት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ወጣቱ ትውልድ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙን ለፅንፈኞች መናጆ ከመሆን እንድትታቀቡ እና ሀገራችን ከወጣቶች የምትፈልገውን ሁሉ ዓቀፍ ተሳትፎ እንድታበረክቱ እጠይቃለሁ።
በሁሉም ዘርፍ ያላችሁ ምሁራን የዳር ተመልካች ከመሆን በዘለለ በምክንያት የሚያምን ትውልድ ይገነባ ዘንድ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ልታበረክቱ ይገባል።
በወጣቶች ደም ውስጥ የከበረች ኢትዮጵያ እንዳለች ሁሉ ወጣቶች የፅንፈኞች መጠቀሚያ ባለመሆን ክልላችሁን እና ሀገራችሁን የሚጠቅም ሁሉ ዓቀፍ ተሳትፎ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።
የአማራ ሕዝብ እናውቅልሃለን በሚሉት የፅንፈኛ አስተሳሰብ ሰለባ በሆኑ ቡድኖች ከጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንደማይደናቀፍ አስረግጠን በመናገር በወንድማማችነት ስሜት የብልጽግናን ራዕይ እውን ለማድረግ ከንጋት እስከ ንጋት በትጋት ከህዝባችን ጋር የምንሰራ መሆናችንን ለማሳሰብ እወዳለሁ።
በመጨረሻም የትንሳኤ በዓልን ስናከብር በቀደመው እሴታችን መሠረት በመረዳዳትና ሌሎችን በመደገፍ ይሆን ዘንድ የድርሻችንን እንወጣ እያልኩ የትንሣኤ በዓል የሰላም እና የጤና እንዲሆን እመኛለሁ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleየክልል ልዩ ኀይሎችን በሁሉም ክልሎች መልሶ የማደራጀት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።