
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከግሬስ ለልጆችና ለቤተሰቦቻቸው ማዕከል እና ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለበዓል መዋያ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
የበዓል መዋያ የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው የትንሳኤ በዓልን እና የኢድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ነው ተብሏል።
የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊዋ የሺአረግ ፈንታሁን እንደተናገሩት ድጋፍ የተደረገላቸው በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ 450 ሰዎች ነው።
ለእያንዳንዳቸውም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር እንደተሰጣቸው ነው የተናገሩት።
ሁሉም ኀላፊነቱን ቢወጣ የተቸገሩ ወገሞችን ማገዝ፣ በዓሉንም በደስታ እንዲያከብሩ ማድግ ይቻላልና ሁሉም ማኅበረሰብ በየአካባቢው የተቸገሩ ወገኖችን እንዲረዳ አሳስበዋል።
የግሬስ ለልጆችና ለቤተሰቦቻቸው ማዕከል ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ አሳብ፤ ድጋፉ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ በማሰብ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራታቸውን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም የተቸገሩ ወገኖች በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችል ድጋፍ እንዳደረገ ነው የተናገሩት።
የድጋፉ ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት “በዓልን በደስታ እንድናከበር ላደረጋችሁልን የገንዘብ ድጋፍ እናመሰግናለን” ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በቦታው ተገኝተው ድጋፉን አበርክተዋል። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲህ ዓይነት ድጋፍ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
“ግሬስ የሁልጊዜም የበጎነት ምሳሌ ነው፣ ለምታደርጉት የበጎነት ተግባር ሁሉ ምስጋና አለን” በማለት ዶክተር ድረስ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!