“የእኛ ቀዳሚ ደስታ ሕዝባችን መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶና ማኅበራዊ እረፍት አግኝቶ ማየት ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

44

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦

እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ!

ትንሳኤ ክርስቶስ ሞትን በትዕግስት አሸንፎ የተነሳበት፤ በአዳም ላይ የተፈረደውን ግፍ እና በደል ሽሮ ፍጹም ደስታና ነጻነት፣ ሰላምና ፍቅር የተገኘበት ነው። መቃብር እና ጨለማ ወደዘላለማዊ ብርሃን የተቀየረበት የጽናት፣ የትህትና እና የፍቅር ተምሳሌት ነው።

ከትንሳኤው ችግርን በትዕግስት አልፈን ለድል መብቃት እንደምንችል እንረዳለን። የእኛ ቀዳሚ ደስታም ሕዝባችን መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶና ማኅበራዊ እረፍት አግኝቶ ማየት ነው። ሕዝባችን በእኩልነትና በፍትህ የሚያምን በመሆኑ መብትና ጥቅሙን ለማረጋገጥ እንሠራለን።

አስተማማኝ ሰላም በሌለበት ደግሞ የምናረጋግጠው እቅድ፤ የምናሳካው የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ፍላጎት አይኖርም። በመካከላችን የሚስተዋሉ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይትና በሰላም መፍታት የምችልበትን ልምድ ማዳበር አለብን።

የአማራ ክልል ሕዝብም የቀጣይ ሕይዎቱን፣ ዘላቂ ሰላሙን፣ የኢንቨስትመንትና የመልማት ጥያቄዎቹን ለማስመለስ በሰላም መፈታት እንዳለባቸው በቀዳሚነት ያምናል። በየትኛውም አግባብ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ያሉ ችግሮቻችንን መፍትሔ ለመስጠት ግጭት ምርጫ አይሆንም።

የሁሉም ፍላጎቶቻችን ስኬት መሠረቱ ህግና ስርዓትን በማስከበር ሰላምን ማረጋገጥ ስንችል በመሆኑ በዓሉን ስናከብር በአስተሳሰብና በተግባር አንድ ሆነን የአካባቢያችን ሰላም የሚያውኩ አላስፈላጊ ጥይት ተኩስና ህገወጥ ተግባራትን በጋራ በመከላከል ሊሆን ይገባል።

ስለሆነም የትንሳኤ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እንድናሳልፍ ጥሪዬን እያቀረብኩ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የአብሮነትና የአንድነት እንዲሆን በክልሉ መንግሥትና በራሴ ስም እመኛለሁ።

መልካም በዓል!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቀዳም ሥዑር (ቅዳሜ ስዑር) – ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብር ያረፈባት ቀን ናት” መምህር ገብረ መድኅን እንየው
Next article“በዓልን በደስታ እንድናከብር ላደረጋችሁልን ድጋፍ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው” ድጋፍ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች