
ፍኖተ ሰላም: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ በመስቀል መከራን ከተቀበለ በኋላ ምሽት 11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ቀበሩት። በዚህም ወደ መቃብር ወረደ።በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን አወጣ።በስጋ ግን ወደ መቃብር ወረደ፡፡እሁድ 10 ሰዓት ከሙታን ተለይቶ ተነሳ።
እለቱም ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ምስራቀ ጸሐይ የመጽሐፍት ትርጓሜ ቤት መምህር ገብርመድኅን እንየው ይናገራሉ።
ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቸ እነሳለሁ ብሎ ያስተማረውን በማሰብ ሶስት ሌሊት ሶስት ማዕልት ቆይተው ነው የተመገቡ። በዚህም የጾም ቀን ተደርጋ ስለምትቆጠር “ስዑር” እየተባለች ትጠራለች ይላሉ።
በዚህች ቀን ሃይማኖታዊ ስርዓቱ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ “ወለመልአከ ሕይዎትሰ ሰቀልዎ ” በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
በዕለቱ የወይራ ቅጠልና እርጥብ ቄጠማ ይዞ ማመስገን አለ። ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ስምንት ላይ ኖህ ውኃው መጉደሉን እርግብን በላካት ጊዜ የወይራ ቅጠል በስንጥሯ ይዛ በመምጣት እንዳበሰረችው ሁሉ በጌታችን ሞትና ትንሳኤ የሀያጢያት ማዕበል፤ የሀጢያት ባሕር ጎደለ። “አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የኖረ የሰው ልጅ በደል ተደመሰሰ” በማለት ካህኑ እርጥብ ቄጤማ ይዞ በመዞር ለምዕመናን ያበስራል።
ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ “ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡
ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው ብለዋል።
በዚሁ ቀን በእለተ አርብ የተከናወነውን የኢየሱስ ክርስቶስ መመርመርና የዲያቢሎስን መታሰር የእለተ አርብ ስርዓቱ ብዙ ስለሆነ በቅዳም ስዑር ካህኑ “ጌታችን ተመረመረ ዲያቢሎስ ታሰረ በማለት ያበስራል።
በዚህ ቀን እነ ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ፣ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከሀጢያት ያነጻቸው ከደዌ የፈወሳቸው ወደ መቃብሩ እየተመላለሱ ያለቀሱበት እለት በመሆኑም ይታሰባል። በአይሁድ ስርዓት የመቃብር ስፍራን ሽቶ መቀባት ባህል ነበርና የጌታችንን መቃብር እየተመላለሱ ከአይሁድ ተደብቀው ሽቶ ይቀቡ ነበር ፣ይህ ስርዓትም ዛሬ በቤተክርስቲያን ታስቦ ይውላል ብለዋል መምህሩ።
ጠዋት ላይ ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ ይጓዛል ሌላው ደግሞ መቋሚያ ይዞ ይከተለዋል።ይህ የሚሆነው ወደ መቃብሩ ስፍራ አይሁድ አላስደርስ ሲሏቸው እያለቀሱ ይሮጡ የነበሩትን ለማስታወስና መቋሚያ ይዞ የሚከተለው ደግሞ ሊመቷቸው ይከተሉ የነበሩትን ለማስታወስ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ቅዳም ሰዑር የሰሞነ ህማማት አንዷ እለት ስትሆን በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ትርጉም ያላት ቀን ናት።
ትንሳኤን ስናከብርም “ሳይታመሙ ህማማትን ሳይሰቀሉ ስቅለትን” ማክበር አይቻልም የሚሉት መምህር ገብረ መድኅን በጌታ ህመሙና በሞቱ ይመስሉት የነበሩትን በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ፣ በመጠየቅና በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ መክረዋል።
ዘጋቢ ፦ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!