የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምስለ ሕክምና ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ።

230

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ደረጃ ሁለተኛ የሆነ የምስለ ሕክምና ማዕከል አስመርቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
ምስለ ሕክምና ማዕከሉ በንድፈ ሐሳብ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የሰመመን ሰጭ (አንስቴዢያ) ሕክምና ትምህርት ለመምህራንና ተማሪዎቻቸው በተግባር የተደገፈ እንዲሆን እድል እንዲፈጥር ታልሞ የተከፈተ ነው። የሰውን አካላዊ ባሕሪ ተላብሰው በተሠሩ አሻንጉሊቶች የታገዘ የተግባር ትምህርት የሚሰጥበት ነው።

ማዕከሉ ‹‹ኢምፓክት አፍሪካ›› በተባለ ድርጅት አማካኝነት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በኢትዮጵያ የተቋቋመ የምስለ ሕክምና ማዕከልም ነው። ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ተገልጿል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ከሕክምናው ክፍል የተወጣጡ አስተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ትናንት ማምሻውን ማዕከሉ ተመርቋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰመመን ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርና የኢምፓክት አፍሪካ አስተባባሪ አቶ ገብረሕይወት አስፋው የማዕከሉ መከፈት የሕክምና ባለሙያዎችን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግና በዘርፉ ያለውን የባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የሕክምና አስተማሪዎችም ሆኑ ተማሪዎች ለታካሚዎች ተገቢውን ሙያዊ አገልግሎት እንዴት መስጠት እንደሚቻል ከማወቅ ባለፈ ብቃታቸውን በተግባር እንዲፈትሹ በር የሚከፍት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በአሜሪካው ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ባንታየሁ ስለሽ ደግሞ በሀገሪቱ ይህን መሰል አገልግሎት መሰጠት መጀመሩ ከባለሙያዎች ልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ለአብመድ አስተያየታቸውን የሰጡ የሕክምና ተማሪዎች ደግሞ የማዕከሉ መከፈት በጋራ የመሥራትና የሕክምና ሙያዊ ባሕልን ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት 15 የሰመመን ሰጭ ሕክምና ተማሪዎችን አስመርቋል። በ2012 የትምህርት ዘመን ደግሞ ከ60 በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

በዓለማችን የተሟላ የሰመመን ሕክምና የሚያገኙት ከ7 ሰዎች 2 ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ ለሰመመን ሕክምና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እጥረት ከሕክምና ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃት ጋር ተዳምሮ ለኅልፈት የሚዳረጉ ሕሙማን መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዘጋቢ :- ሀይሉ ማሞ

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት ከሕግ አስፈጻሚ፣ ሕግ ተርጓሚ አካላትና ከሕዝብ ክንፍ መሪዎች ጋር እየተወያዬ ነው፡፡
Next articleየቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ ከእስር ሊፈቱ ይችላል ተባለ፡፡