
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔ በዓል በኩረ በዓላት፣ የበዓላት ሁሉ አለቃ እንደኾነ የዕምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ። በባሕር ዳር ሀገረስብከት የቅዱስ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን አሥተዳዳሪ መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ እንዳሉት የትንሣዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት መከራን የተቀበለበት፣ በመከራም ፍቅር፣ ትሕትናና ትዕግስትን ያስተማረበት፣ ሞትንም ድል አድርጎ የተነሳበት ነው።
የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን መነሳት ብቻ የሚዘክር ሳይኾን የእኛም ከሃጢአያት መነሳት የሚሰበክበት እንደኾነም ያስረዳሉ። ትንሣዔው ካለማወቅ ወደ ማወቅ፣ ከመጥፎ ነገሮች ወደ መልካም እሳቤዎችና ድርጊቶች ሁሉ የምንጓዝበት ነው።
በዓሉ በደስታ የምናከብረው በዓል ነው ያሉት መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገልን ኹሉ ዋጋን መክፈል የሚቻለው የተቸገሩትን በመርዳት፣ ላዘኑት አለኝታም በመኾንም ጭምር ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ደስታ የሚገኘው በበዓሉ ዕለት በመብላት፣ በመጠጣት ብቻ አይደለም፣ በመስጠትም ነውና የሌሎችን ጉድለት በመሙላት የደስታቸው ምክንያት መኾን ተገቢ ነው ብለዋል።
በመስጠት ላይ የተመሰረተ ደስታ ነፍሳዊ፣ በመቀበል ላይ የተመሰረተው ደስታ ደግሞ ሥጋዊ ነው የሚሉት መልዓከ ምሕረት ግሩም መተባባር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መደጋገፍ እና የተቸገሩትን ማስታወስ የሃይማኖቱ ዐቢይ አስተምህሮ መኾኑን ይጠቅሳሉ። የደስታ በዓል ነውና በዕለቱ የተቸገሩትን በማገዝ ከአዘኑበት፣ ከተከፉበት፣ ከችግራቸው ወጥተው በዓሉን በደስታ በፍቅር እንዲያከብሩ ማስቻል ከአንድ አማኝ በእጅጉ የሚጠበቅ መኾኑን ያሳስባሉ።
ለተቸገሩት መድረስ አይዟችሁ ማለት፣ የተስፋ መንገድ ማሳየት፣ የማንቃት ወንጌል መስበክ እንደኾነም ነው የተናገሩት። “በዓሉን ስናከብር የሃይማኖቱን አስተምህሮ በተግባር በመፈጸም መኾን አለበት” ነው ያሉት መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ።
በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሰዋዊ ግንኙነትን፣ ሰው እንዳይቸገር መደገፍን ከንግግር በላይ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የምትሰብከው ነው ሲሉም ያስረዳሉ።
“ክርስቶስ ተነስቷል፤ በክርስቶስ መነሳት እኛም እንደምንነሳ እርግጠኞች ኾነናል፤ በሕይወት እያለን የሕሊና መነሳት ያስፈልገናል” እያለች ቤተክርስቲያን ትሰብካለች ይላሉ መልዓከ ምሕረት ግሩም። የሕሊና መነሳት ማለት ደግሞ መልካሙን ነገር መከተል፣ መጥፎውን መተው እንደኾነም መረዳት ይገባል ነው ያሉት። በዓሉን ተከትለው የሚደረጉ ከልክ በላይ መጠጣት፣ ዘፈኑ እና ዳንኪራው ክርስቲያናዊ ከኾነው የበዓል አከባበር መውጣት ነውና በዓሉን ዕምነቱ በሚፈቅደውና በሚያዘው መሠረት ማክበር ተገቢ ነው ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔ በዓል የፍቅር፣ የደስታና የመተሳሰብ እንዲኾን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!