
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባውን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በሜዳህ ድሔ፣ በመስቀል ላይ ተሠቅየ፣ አድንሃለሁ ብሎ የገባለትን ቃል ለማክበር ወደዚች ምድር በመጣ ጊዜ አይሁድ ልባቸው ታውሮ ነበርና የተናገረውን ሁሉ አልተቀበሉትም፡፡ እንዴት ከምናውቃቸው ከእያቄም እና ከሃና ከተወለደችው ከማርያም የተወለደው ብላቴና አምላክ ነኝ ብሎ ያታልለናል በማለት ይከታተሉትም ነበር፡፡
ይህ ሰው ሰንበትን ሽሯል፤ የሞተ አስነስቷል፤ እውር አብርቷል ብለው ከሰሱት፡፡ በዚህም ከሰው ጲላጦስ ፊት በአደባባይ ለፍርድ አቆሙት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመሰቀል ያበቃው ኃጢአቱ ይህ ነበር ብለዋል የቅኔ እና የአዲስ ኪዳን መምህሩ ጥቀኄር ወርቄ፡፡
ጲላጦስም ነገሩን መርምሮ እንኳንስ ለመስቀል ለመግረፍ የሚያበቃ ኃጢአት አላገኘሁበትም ብሎ ገርፎ ሰጣቸው፡፡ በሀገሩ ሕግ የተሠቀለ አይገረፍም፣ የተገረፈም አይሠቀልም ነበር። አይሁድም ኢየሱስን አምርረው ጠልተውታልና” ገርፈው ሊለቁት አልፈቀዱም በቃ ይሠቀል ብለው ደመደሙ፡፡ ሰዓቱም አንድ ሠዓት ነበር፡፡
መስቀል ተሸክሞ ተራራ ሲወጣ በየተራ ይገርፉት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ሠዓት ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዓት ጉዞው ወደ ቀራንዮ ነበር፡፡ ወደ ቀራኒዮ ያመራበትም ምክንያት ሲያስረዱም ቀራንዮ የአዳም አጽም ያረፈባት ቦታ በመኾኗ ክርስቶስ የአዳምን በደል ሊሽር ወደዛው አመራ ብለዋል የቅኔ እና የአዲስ ኪዳን መምህሩ መምህር ጥቀኄር ወርቄ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀራንዮ ሲያቀና አይሁድ ጠልተውታል እና የሚሰቀልበትን እርጥብ እንጨት አመሳቅለው አሸከሙት፡፡ እየተፈራረቁም ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ግርፋት ገረፉት፡፡
መስቀል ተሸክሞ ተራራ ሲወጣ ይገርፉት ነበረ በየተራ እንዳለ ባለቅኔው። ከአራት አቅጣጫም በገመድ አስረው ይጎትቱት ነበር፣ የፊተኛው ሲጎትተው በፊቱ ይወድቃል፣ የኋለኞቹ ይረግጡታል፣ገርፈው ያስነሱታል፤ የኋለኞቹ ሲጎትቱ በጀርባው ይወድቃል፣ የፊተኞቹ የትገባ ብለው በልቡ ላይ ይቆሙበታል፤ ወደቀኝ ወደ ግራ እየጎተቱ እየጣሉ እያስነሱ መስቀሉን እያሸከሙ አብዝተው ገረፉት፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ግርፋት ለማስቀረት ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ጊዜ ተገረፈ፡፡ ከግርፋቱ የተነሳ ክርስቶስ በስጋው ደከመ ይኼኔ የክርስቶስ ወዳጅ ስሞን የሚባል ሰው ጠርተው መስቀሉን አሸከሙት፡፡ ይህንን እያሠቡ ነው የእምነቱ ተከታዮች በስግደት ሲወድቁ ሲነሱ የሚውሉት ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!