
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእለተ አርብ በነገረ መስቀሉ ስለሆነው የቅኔ እና የሐዲስ ኪዳን መምሕሩ ጥቀኄር ወርቄ ሲያብራሩ እንዳሉት ፀሐይ ብርሃኗን ከለከለች፣ ከዋክብት ረገፉ፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፡፡ ምድር ተናወጸች፣ ቀላያት ተከፈቱ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መጋረጃ ከሁለት ተቀደደ፡፡ የ5 ሺህ 500 ዘመን የአዳም ልጆች መከራ እና ፍዳ ፍጻሜ ተቃረበ፡፡ አዳም ሊመረመር ዲያቢሎስም ሊታሰር ተቃርቧልና ሊነጋ ሲል ጨለመ፡፡ ትዕቢተኞች ከትዕቢታቸው፤ ትሁታን ከትዕግስታቸው የሕይወትን ፍሬ የሚያዩበት ቀን ደረሰ፡፡ መወለዱን አይተው እረኞች በቤተልሄም እንደዘመሩ ሁሉ ከሞቱ በኋላ በቀራኒዮ አደባባይ ተዓምራትን ያዩ ሁሉ ደነገጡ፡፡
የሰውን ልጅ ሃጢአት እና ሃፍረት ለማስወገድ በባህሪው ሃጢአት፤ በመንግሥቱም ሃፍረት የሌለበት እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ተሰቀለ፡፡ ከመወለዱ 100 ዓመታትን ቀድመው ስለመወለዱ ነብያት በትንቢት ተናግረዋል፡፡ ከነብዩ ዳዊት እስከ ነብዩ ኢሳያስ የሰው ልጅ ሲሉ የሚጠሩት ክርስቶስ ኢየሱስ ከልደቱ እስከ ሞቱ፤ ከእርገቱ እስከ ዳግም ምጽዓቱ የሚሆነውን እና የሚሆንበትን ሁሉ ተናግረው ነበር፡፡ ከተነገረው የጎደለ፣ ከተገለጠው የተሰወረ እና መሆን ከነበረበት ያልሆነ ምንም ነገር አልነበረም፡፡
አውግስጦስ ቄሳር የሮም ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ ትልቁ ሔሮድስም ይሁዳን ይገዛበት በነበረበት ጊዜ ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወለደችው፡፡ የእግዚአብሔርን መሲ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ የገለጸለት አረጋዊው ስምኦን “ዐይኖቼ በእርግጥ ማዳንህን አይተዋልና ባሪያህን እንደቃልህ በሰላም ታሰናብተዋለህ” ሲል ቀድሞ በነብያት ትንቢት የተነገረለት የሰው ልጅ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ስለመወለዱ ምስክር ሆነ፡፡ እንደ መላኩ ብስራትም ስሙ ኢየሱስ ተባለ፡፡
በንጉሥ ጢባሪዮስ በ15ኛው የግዛት ዘመን፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ አሥተዳዳሪ ሳለ፣ ሔሮድስም የገሊላ አውራጃ ገዢ በነበረበት ወቅት፣ ሐናና ቀያፍም ሊቀ ካህናት ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መንገድ ጠራጊው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ መጣ፡፡ በነብዩ ኢሳያስ ትንቢት “ሥጋ የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል” እንደተባለ ክርስቶስ ኢየሱስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ በእርግብ አምሳል መጥቶ “የምወድህ ልጀ አንተ ነህ፤ በአንተም ደስ ይለኛል” ሲል አረጋዊው ስመኦን በልደቱ እንደመሰከረለት ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀቱ ፍጹም አምላክ መሆኑን ከሰማይ መሰከረ፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር እድሜው 30 ዓመት አካባቢ ነበር፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ መንፈስ ቅዱስ የተሞላው ክርስቶስ ኢየሱስ በምድረ በዳ 40 ቀናትን ተፈተነ፡፡ የዲያቢሎስን ፈተና በጽናት፣ መከራውን በጸሎት ድል አድርጎም ወደአደገበት ወደ ናዝሬት ተመለሰ፡፡ በፍጹም ፍቅር እና በፍጹም ትህትና የሰውን ልጅ በደል ለመካስ ሃጢአቱንም ለመደምሰስ መከራና ግፍ፣ ግርፋት እና ስቅላት፣ መወጋት እና መንገላታት ሁሉ ከዚህ ጊዜ ይጀምራሉ፡፡
ኢየሱስ በቤተ መቅደስም ሳለ ከነብዩ ኢሳያስ የመጽሐፍ ቃል እንዲያነብ ጋበዙት፡፡ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ወንጌልን ለድሆች እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፡፡ ለታሰሩ መፈታትን፤ ለእውሮችም ማየትን አውጅ ዘንድ ልኮኛል፡፡ የተጠቁትን ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውን የጌታን ዓመት ለሕዝቡ እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” ዛሬ የዚህ መጽሐፍ ቃል እንደሰማችሁት ተፈጸመ ቢላቸውም አይሁድ ግን እንደ መሲህ አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ኢየሱስም ሰዓቱ አልደረሰምና “ነብይ በሀገሩ አይከበርም” ብሎ ተለያቸው፡፡
በመንገዱ ሁሉ ቸርነትን በአስተምህሮው ሁሉ ሕይዎትን የሚያድለው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ከተማ ቅፍርናሆም አመራ፡፡ ለስምኦን የዓሳ በረከትን እንዳደለ ሁሉ ለኢያሂሮስም ልጁን ከሞት ወደ ሕይዎት መለሰለት፡፡ እያዩ የማያምኑ፣ እየተናገራቸው የማያስተውሉ፣ እየተደረገላቸው የማያመሰግኑ ቢኖሩም ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ትምህርትን ከሕይዎት፤ ምሕረትን ያለስስት ያደርግ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ በሞገስ እና በክብር ያደገው ኢየሱስ ቀስ በቀስ ሰሞነ ሕማማትን አገባድዶ ወደ ዓርብ ደረሰ፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስ ለአዳም “በእኔ ደም ወደ ገነት ትመለሳለህ” የሚል ቃል ኪዳን ሰጥቶት ነበር ያሉን የቅኔ እና የሀዲስ ኪዳን መምሕሩ ጥቀኄር ወርቄ የአዳም የእዳ ደብዳቤ በደም የሚታጠብበት እና የሚነጻበት ቀን ዓርብ ነበር ይላሉ፡፡ መጽሐፍ “ከአመጸኞች ጋር በአንድነት ተቆጠረ” እንዳለ ክርስቶስ በቀኝ እና በግራው ከወንበዴዎች ጋር እንደ ወንበዴ ተሰቀለ፡፡ ከስቅለቱ ቀድሞ ከዘመነ ፍዳ ጋር የማይነጻጸር መከራ እና ስቃይን ሁሉ አይቷል የሚሉት መምህር ጥቀኄር በመስቀል ላይ ሳለ “ሁሉ ተፈጸመ!” አለ ይሉናል፡፡
ሁሉ ተፈጸመ ሲባልም የመጀመሪያው የተፈጸመው አዳም ከገነት ተባርሮ በደብር ቅዱስ ይኖር ነበርና በእኔ ደም ትመለሳለህ ወደተባለበት ገነት ተመለሰ፡፡ ነብዩ ኢሳያስ ቀድሞ “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” እንዳለ በቁስሉ ገነትን በሞቱ ድኅነትን አግኝተናል ይላሉ መምህር ጥቀኄር ወርቄ፡፡ ሌላው የተፈጸመው ግን ቀድመው ነቢያት ከተናገሩት ሁሉ የቀረ አለመኖሩን ሲያረጋግጥልን ነው ብለውናል፡፡ አይሁድ ከጎናቸው የተፈጠረውን መሲህ እንደመሲህ መቀበል ቢሳናቸውም ተፈጸመ ብሎናልና ሁሉም ተፈጽሟል፡፡
ዛሬም እኛ የትንሣኤው እድለኞች የስቅለቱ አማኞች በተሰቀለች ሀገር ውስጥ ነን የሚሉት መምህሩ አርብ የመከራ፣ የግርፋት፣ የመሰደድ እና የመሳደድ ቀን ቢሆንም እሁድ ትንሣኤ እንዳለ አምነን በጾም እና ጸሎት፣ በስግደት እና በንስሃ ትንሣዔዋን መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ በስቀለት ላይ ያለችን ሀገር ወደ ትንሣዔዋ የሚያሸጋግሩ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚሉት መምህሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሀገሩ፣ ስለሕዝቡ እና ስለሃይማኖቱ በአንድ መቆምና መጽናት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!