
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “በበገና መሳሪያ ፈጣሪን ማመስገን የመንፈስ መታደስንና መረጋጋትን ይፈጥራል” ይላሉ የቅዱስ ያሬድ የበገና ማሰልጠኛ ማእከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ታደሰ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፡፡
በገና በጾም፣ በጸሎት፣ በምስጋና፣ በሐዘንና በእንጉርጉሮም ጭምር የሚዜምበት መንፈሳዊ መሳሪያ እንደኾነ ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚለው መጽሐፋቸው “በገና በቁሙ መዝሙር ማለት ነው” የሚል ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡
የተለያዩ የመረጃ ምንጮች በገና መቼ አገልግሎት ላይ እንደዋለ የተለያየ ጊዜ ቢጠቅሱም ዓላማው ላይ ግን አንድ አይነት ማብራሪያ አላቸው፡፡ “በገና ትልቅ የጥሞና፣ የጸሎትና የምስጋና መንፈሳዊ መሳሪያ” ስለመኾኑ ነው የሚያስረዱት፡፡
የቅዱስ ያሬድ የበገና ማሰልጠኛ ማእከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ታደሰ ስለ በገና የምስጋና መሳሪያ አገልግሎት ሲገልጹ በገና መጀመሪያ መላእክት ያመሰገኑበት፣ ቀጥሎም ዳዊት ያመሰገነበትና ከጥንት እስከዛሬም ለመንፈሳዊ ምስጋና እያገለገለ የሚገኝ ትልቅ መንፈሳዊ መሳሪያ ነው ይሉታል፡፡
አማኞች ቃላትን እየደረደሩ በግጥም፣ የበገና አውታሮችን እየደረደሩ በዜማ አምላካቸውን፣ ድንግል ማሪያምን እና የፈለጉትን ሁሉ ያመሰግኑበታል ነው ያሉት፡፡
በገና እንደየሁኔታው የሐዘን፣ የእንጉርጉሮ፣ የንስሐ፣ የጸሎት፣ የልመናና የምስጋና መሣሪያ እንደኾነም ነው የሚያስረዱት፡፡
ሁሌም ምስጋና፣ ሁሌም ጸሎትና ልመና እስካለ ድረስ በበገና ማመስገንና መጸለይ እንደሚቻል ነው ባለሙያው የሚናገሩት፡፡
በተለይ በዐቢይ ጾም የበገና አገልግሎት ሲዘወተር ማየት የተለመደ በመኾኑ በገና በጸሎተ ሐሙስ ሰሞንና በአጽዋማት ወቅት ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውል አስመስሎታል ይላሉ፡፡
በገና በዋናነት ለመለኮታዊ ፈቃድ ማስፈጸሚያ ማለትም ለምስጋናና ለልመና የሚያገለግል እንደመኾኑ ሁሉም ለበገና የቀረበ ልምምድና አገልግሎት እንዲኖረው ይመክራሉ፡፡
“በበገና መሳሪያ ፈጣሪን ማመስገን የመንፈስ መታደስንና መረጋጋትን ይፈጥራል” ነው የሚሉት፡፡
በገናን ተምሮ፣ አውቆ እየደረደሩ፣ እያዜሙ አገልግሎቱን መጠቀም፣ በገናን በሌሎች ባለሙያዎች በካሴት ተቀርጾ ከማድመጥ የበለጠ ልዩ ጥሞናንና የመንፈስ መታደስን የሚሰጥ፣ ጸሎትንና ምስጋናን ለአምላክ ለማድረስ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
እንደባለሙያው ማብራሪያ በገና በጸሎት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ይመሰገንበታል፣ ቅዱሳን ይመሰገኑበታል፣ ሌሎች ጉዳዮችም እየተነሱ ይወደሱበታል ይሰበኩበታል፡፡ በገና በጥሞና የሚዜም ልቦናን የሚሰበስብ ድንቅ መሳሪያ ስለመኾኑም ነው የሚያስረዱት፡፡
ከፍተኛ የመንፈስ መረጋጋትን የሚፈጥረው በገና ቅዱስ ዳዊት አምላኩን እንዳመሰገነበትና ከፈጣሪው ጋር በጸሎት ይነጋገርበት እንደነበር መንፈሳዊ መጽሐፍት ያስረዳሉ፡፡
በገና ካለው አገልግሎትና ጥቅም አንጻር አሁን ላይ አገልግሎቱን ተሻጋሪ ለማድረግ የማስልጠኛ ካሪኩለም እየቀረጹ የሚያስተምሩ አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ሁሉም ሰው በገናን ለሚገባው አገልግሎት ማዋል አለበት የሚሉት ባለሙያው የበገናን ቅርጽ የያዙ ሌሎች ቁሳቁሶችን፣ መቀመጫ ወንበሮችን እያሠሩ ለክብሩ በማይመጥን ቦታ ላይ ማዋል እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!